ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ መንግስት የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ያለውን አቋም መረዳት ችለናል-ነዋሪዎች

74

ሶዶ የካቲት 15/2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በፓርላማ ካቀረቡት ማብራሪያ መንግስት የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ለማስከበር ያለውን አቋም መረዳት ችለናል ሲሉ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው በሀገር የማፍረስ ጦርነት እጃቸው አለበት ተብሎ በህግ ቁጥጥር ስር የነበሩ የተወሰኑ እስረኞችን የክስ ሂደት አቋርጦ በመፍታቱ ህዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን ብዥታ የሚያጠራ ምላሽ ሰጥተዋል" ሲሉ ነዋሪዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ3ኛው አስቸኳይ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከአባላቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ መስጠታቸው ይታወቃል።

መንግስት የተወሰኑ እስረኞችን በመፍታቱ ጥያቄ ፈጥሮባቸው እንደነበር የተናገሩት የከተማው ነዋሪ አቶ አድማሱ ከበደ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ምላሽ ብዥታቸው እንደጠራ ገልጸዋል።

"ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስረኞቹ ከተፈቱ በኋላ ኢትዮጵያ በርካታ ጥቅሞች እንዳገኘች መናገራቸው የክስ ማቋረጥ ሂደቱ የሀገሪቱን ጥቅም በተለያዩ መንገዶች ያስከበረ መሆኑን ግልጽነት እንድኖረው አድርጓል" ሲሉ ገልጸዋል።

እስረኞች መፈታታቸው ህጋዊ መሠረት ያለው መሆኑን በማብራሪያው ማወቃቸውን ጠቁመው የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ መደረጉን ከምላሻቸው በመስማታቸው በጉዳዩ ላይ የጠራ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ሞገስ መርዕድ በበኩላቸው "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊደረግ ከታሰበው አገራዊ ምክክር ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ ድርድር እንደማይደረግ መናገራቸው በሂደቱ ላይ የነበሩ ስጋቶችን የሚቀርፍ ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአገራዊ ምክክር መድረኩ ጋር ተያይዞ እድሉን እንዲጠቀሙበት ለተፎካካሪ ፓርቲዎችና የአቋም ልዩነት ላላቸው አካላት ያቀረቡት ጥሪ የሚደነቅ መሆኑን አመላክተዋል።

አክለውም "ድርድሩ ዜጎችን ካለፉና ከማይጠቅሙ ትርክቶች በማውጣት የተሻለ መግባባት ላይ ሊያደርስ እንደሚችል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ተስፋን ሰንቄያለሁ" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ በየቦታው እያየለ የመጣውን የሌብነት ተግባር ለመቀነስ ጉበኞችና ሌቦች እጃቸውን እንዲሰበስቡ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸው ይበል የሚያሰኝ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ወጣት ተካልኝ አበራ ነው።

"ጠቅላይ ሚኒስትሩ መገናኛ ብዙሀን በሌብነት የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የሚያስችሉ  የምርመራ ዘገባ እንዲሰሩ ማበረታታቸው ብዠታን ከማጥራት በበለጠ ዜጎች በመንግስት ላይ ተስፋና ዕምነት  እንዲጥሉ የሚያደርግ ነው" ሲል ወጣት ተካልኝ  ገልጻል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም