ከኢትዮጵያ ነዳጅ ጭኖ ወደ ውጭ አገራት የሚወጣ ተሽከርካሪ ነዳጁም ተሽከርካሪውም ሊወረስ ይገባል

69

የካቲት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከኢትዮጵያ ነዳጅ ጭኖ ወደ ውጭ አገራት የሚወጣ ተሽከርካሪ ከተገኘ ነዳጁንም ተሽከርካሪውንም ሊወረስ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያውያን በኮቪድ ወረርሽኝ፤ በውስጣዊ የሰላም እጦትና በምዕራባውያን ጫና እንዲሁም የዓለም የሸቀጦች የዋጋ መጨመር ምክንያት በኑሮ ውድነት እየተፈተኑ መሆኑን አንስተዋል።

ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን፤ የምርት ዋጋ ይጨምራል በሚል ሰበብ ምርት መደበቅና ሸማቹ በውድ መግዛት የኑሮ ውድነት አባባሽ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዓለም ገበያ የምግብና ሌሎች ተያያዥ ሸቀጦች ዋጋ መጨመር የኑሮ ውድነትን በማባባስ የዜጎችን ህይወት እየተፈታተነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ለዓብነት ማዳበሪያ 176 በመቶ፣ ብረት 65 በመቶ፣ ነዳጅ 85 በመቶ፣ ስኳር 35 በመቶ፣ የምግብ ዘይትና የማጓጓዣ ኮንቴነር በ285 በመቶ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ማሳየታቸውን ጠቅሰዋል።

መንግስት ችግሩን በዝምታ አልተመለከተውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር የሚያስችሉ እርምጃዎችን ወስዷል ብለዋል፡፡

አቅርቦቱን በመጨመር የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ለምግብ ሸቀጥ 1 ቢሊዮን ዶላር ወጭ የተደረገ ሲሆን ዘንድሮ ከአምናው ተመሳሳይ ወራት እጥፍ ጨምሮ 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ወጭ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

በመንግስት ድጎማ አማካኝነት በኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ከጎረቤት ሀገራት ቅናሽ በማሳየቱ አንዳንድ ስግብግብ ባለሃብቶች ከውጭ ያመጡትን ነዳጅ ወደ ጎረቤት አገራት እንደሚሸኙ ተደርሶበታል ብለዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ የነዳጅ አቅርቦት እጥረትና ውድ እንዲሆን አድርጎታል ነው ያሉት።

በመሆኑም ነዳጅ ከኢትዮጵያ ወደ ጎረቤት አገራት አጓጉዘው የሚሸጡ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ የጸጥታ ሃይሎች ጥብቅ ቁጥጥር ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

በዚህ ድርጊት ላይ ተሳታፊ በመሆን ከኢትዮጵያ ነዳጅ ጭኖ በመውጣት ወደ ሌሎች አገራት የሚወጣ ተሽከርካሪ ነዳጁም ተሽከርካሪውም ሊወረስ ይገባል ብለዋል።

በሁሉም ክልል የሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች እንዲህ አይነት ወንጀሎችን እንዲቆጣጠሩ እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም