የመገናኛ ብዙሃን የምርመራ ዘገባዎችን በስፋት በመስራት ሌቦችን ማጋለጥ አለባቸው

152

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15/2014 (ኢዜአ) የመገናኛ ብዙሃን የምርመራ ዘገባዎችን በስፋት በመስራት ሌቦችን ማጋለጥ እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አሳሰቡ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያካሄደ ባለው 3ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከምክር ቤት አባላት በኢትዮጵያ ሌብነት ከባድ ፈተና ሆኗል፤ በእጅጉም ተስፋፍቷል፤ መንግስት ለመከላከል ምን አስቧል በማለት ተነስቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያም ሌቦች በተበራከቱበት አገር ስለ እድገት ማሰብ ቀርቶ አብሮ መሆን ከባድ ፈተና ይሆናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ያልተገባ ሃብት የሚያግበሰብሱ ግለሰቦች ባለስልጣንንም ጭምር ሌባ በማድረግ እንደፈለጉ ለማዘዝ የሚሹ መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ እየተበራከተ የመጣውን ሌብነት ለመዋጋት በተለይም መገናኛ ብዙሃን የምርመራ ዘገባዎችን በስፋት በመስራት ሌቦችን ማጋለጥ አለባቸው ብለዋል።

ከመገናኛ ብዙሃን በተጨማሪ አጠቃላይ ማህብረሰቡ ሌቦችን ማጋለጥና ሌብነትን የሚፀየፍ መልካም ዜጋ ማፍራት ላይ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም