ሀገራዊ የምክክር መድረኩ የማህብረሰቡን ባህላዊ እሴት መሠረት አድርጎ ሊካሄድ ይገባል-ምሁራን

111

ጂንካ ፤የካቲት 15/2014 (ኢዜአ) ሀገራዊ የምክክር መድረኩ የማህብረሰቡን ባህላዊ እሴት መሠረት አድርጎ ሊካሄድ ይገባል ሲሉ የጂንካ፣ ዲላ እና የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ገለጹ።

የጂንካ ዩኒቨርስቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤሊያስ አለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት በየደረጃው የሚካሄደው የምክክር መድረክ ውስብስብ ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ መፍትሄ የሚያስገኝ ነው።

 በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ የመስራት ባህልን ለማጎልበት ፋይዳው የጎላ  እንደሆነ ጠቁመዋል።

መድረኩ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉም ወገን በሰከነ መንገድ ሀሳቡን በነፃነት ለማቅረብና ለመሟገት የሚያስችል መሆኑን የጠቆሙት ምሁሩ፤ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የሚያስችል አጋጣሚ  በመሆኑ እድሉን በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

"በሀገራዊ የምክክር መድረኩ አለመግባባቶችን ለመፍታትና እልባት ላይ ለመድረስ የመደማመጥ እና በሀሳብ የበላይነት የማመን ልምዳችንን ማሳደግ አለብን" ብለዋል።

 በሀገሪቱ ከሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦች ቱባ ባህላዊ እሴቶች ልምድ በመቅሰም  ለምክክር መድረኩ ስኬታማነት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ  ዶክተር ፈቀደ ምኖታ በበኩላቸው የምክክር መድረኩን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ሀገራዊ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚቻል ገልጸዋል።

''የምክክር መድረኩ የአመራሮችና የፖለቲካ ሊህቃን የድርድር መድረክ ብቻ ሊሆን አይገባም'' ያሉት ዶክተር ፈቃደ፤  የምክክር መድረኩ ስኬታማ እንዲሆን ማህበረሰቡን ያሳተፈና ባህላዊ እሴቱን የጠበቀ  ሊሆን  እንደሚገባ አመልክተዋል።

የምክክር መድረኩ በሚካሄድበትም ወቅት ከትንንሽ ችግሮች በመነሳትና እያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማወያየት ወደ ትላልቅና ውስብስብ ችግሮች መሄድ ውጤታማ እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጀ  ክፍሌ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት አለመኖር በማህበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ምስቅልቅል ያስከትላል ብለዋል።

ይህ እንዳይከሰትና አካታች ምክክሩም ፍሬያማ እንዲሆን  የምክክር ኮሚሽኑን የሚመሩ አካላት ከሌሎች ሀገራት ልምድና ተሞክሮ በመቅሰም ለተፈጻሚነቱ ሊተጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በህዝብ የተመረጡ ኮሚሽነሮች  የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ይበልጥ በማጠናከርና ሀገራዊ አንድነት በማምጣት የበለፀገችና የምንናፍቃትን ሀገር እንድናይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ዶክተር ደረጀ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ምሁራን ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸው "በተለይ ትክክለኛና ተጨባጭ ባልሆኑ መረጃዎች የሚደረገውን ፍረጃ ሊያርሙ ይገባቸዋል" ብለዋል።

ህዝቡን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ በመምራትና  በእውቀት ላይ የተመሰረተ እውነትን በመያዝ መሞገትና ማሳመን እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን የሚመሩት 11 ኮሚሽነሮች ዝርዝር ለምክር ቤቱ ቀርቦ ምክር ቤቱ ትናንት  ባካሄደው ሁለተኛ አስቸኳይ ስብሰባ በአምስት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ  ሹመታቸውን ማጽደቁ ተመላክቷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባት ለመፈጠር ያስችላል የተባለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1265 /2014 ማጽደቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም