በመስኖ ለምቶ ለገበያ እየቀረበ ያለው ምርት ለዋጋ መረጋጋት እያገዘ ነው

152

ባህር ዳር ፣ የካቲት 15/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በበጋ ወራት በመጀመሪያው ዙር መስኖ ለምቶ ለገበያ እየቀረበ ያለው ምርት ዋጋ ለማረጋጋት እያገዘ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ በመጀመሪያው ዙር መስኖ እስካሁን ከ220 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መልማቱ ተመልክቷል።

በቢሮው የሰብልና ኢንዱስትሪ ምርቶች ግብይት ዳይሬክተር አቶ ልንገረው አበሻ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ከመኽር ሰብል በተጨማሪ በበጋ በመስኖ የሚመረተው ለገበያው መረጋጋት አዎንታዊ ድርሻ አለው።

ዘንድሮ በመጀመሪያ ዙር መስኖ የለማው የጓሮ አትክልት በአሁኑ ወቅት ለገበያ መቅረብ በመጀመሩ የዋጋ ንረቱ እንዲረጋጋ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በኪሎ እስከ 30 ብር ሲሸጥ የቆየው ቀይ ሽንኩርት ወደ 20 ብር፣ ድንች ከ25 ብር ወደ 19 ብር፣ ቲማቲም ከ28 ብር ወደ 24 ብር በአማካኝ እንዲቀንስ ማገዙን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ምርቱ በስፋት ወደ ገበያ መቅረብ ሲጀምር ዋጋው የበለጠ እንደሚረጋጋ አመልክተዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት በተለይ አሸባሪው ህወሓት በምስራቅ አማራ በፈፀመው ወረራ ያጋጠመውን የግብርና ምርት ዕጥረት ለማቃለል ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በገበያ ትስስር ወደ አካባቢው ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

እስካሁን በተቋቋሙ 279 የአርሶ አደር የግብይት ቡድኖች፣ በማህበራትና በጅምላ ነጋዴዎች በኩል ከ490 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለህብረተሰቡ መቅረቡን አስታውቀዋል።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ ውሃ አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ወንድምነው በበኩላቸው፣ በክልሉ በመጀመሪያ ዙር 220 ሺህ 413 ሄክታር መሬት በመስኖ መልማቱን ገልጸዋል።

በአንደኛና ሁለተኛ ዙር የመስኖ ልማት ከ1 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉ ገልጸው፣ በሁለት ዙር ከሚለማው 51 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።

"እስካሁን የምርት መሰብሰብ በተጀመረባቸው አካባቢዎች ሽንኩርትን ጨምሮ ከ2 ሚሊዮን 148 ሺህ ኩንታል በላይ የአትክልት ምርት ለገበያ መቅረብ ጀምሯል" ብለዋል።

በመስኖ ከሚያለሙት ምርት በዓመት እስከ 50 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በአዊ ዞን አንከሻ ወረዳ የጥርባ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሞላ ጌታቸው ናቸው።

ዘንድሮም ግማሽ ሄክታር ከሚጠጋ መሬት በመስኖ ያለሙትን ሽንኩርት፣ ቃሪያና ድንች ወደ ገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ከምርት ሽያጭ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተስፋቸውን ገልፀዋል።

በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ የይጎማ ሁለቱ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ብርሃን አሰፋ በበኩላቸው በየዓመቱ በሦስት ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ ከሚያለሙት እስከ 200 ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኙ አመልክተዋል።

"ዘንድሮም እያለማሁት ካለው ሽንኩርትና ሸንኮራ አገዳ የተሻለ ገቢ አገኛለሁ ብዬ እጠብቃለሁ" ብለዋል።

በባህር ዳር የጣና ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ የእናትፋንታ መሃሪው በበኩላቸው በምርት አቅርቦት እጥረት ዋጋቸው የጨመረው ሽንኩርትና ቲማቲም በአሁኑ ወቅት እየቀነሱ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ምርቱ ወደ ገበያ መቅረብ በመጀመሩ በኪሎ ከአምስት እስከ 10 ብር ቅናሽ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ባለፈው ዓመት በመስኖ ከለማው 230 ሺህ ሄክታር መሬት 37 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም