በእሳት አደጋ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ የሦስት ሕፃናት ሕይወት አለፈ

361

ሆሳዕና ፤ የካቲት 15/2014 (ኢዜአ) በስልጤ ዞን ሚቶ ወረዳ ድንገት በተከሰተ የእሳት ቃጠሎ አደጋ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ የሦስት ሕጻናት ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

አደጋው የደረሰው በወረዳው “ግርንዝላ ሸፎዴ”  የገጠር ቀበሌ ትናንት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል አካባቢ መሆኑን የሚቶ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር አክመል ከይረዲን ገልጸዋል።

በዚህም  በመኖሪያ ቤት ውስጥ የነበሩ የስድስት፣ የአምስት እና የአንድ ዓመት ዕድሜ ያላቸው የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ ሦስት ህፃናት  ሕይወታቸው ማለፉን አስታውቀዋል።

ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ ሴቶች እንደሆኑ አመልክተዋል።

የእሳት አደጋው ሁለት መኖሪያ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ሲያወድም በቤት ውስጥ የነበሩ አምስት የቤት እንስሳትንና ሌሎች ንብረቶችን ማውደሙንም ኢንስፔክተር አክመል ተናግረዋል።

በተጨማሪ በግቢ ውስጥ የነበረና ለጊዜው ግምቱ ያልታወቀ የበቆሎ፣ ገብስ እና የጥራጥሬ እህል ማውደሙን አመልክተዋል።

“የአካባቢው ህብረተሰብ የእሳት ቃጠሎው ለማጥፋት ባደረገው ርብርብ ወደሌሎች ቤቶች እንዳይዛመትና ተጨማሪ አደጋ እንዳያደርስ ለማድረግ ተችሏል” ብለዋል።

የወረዳው የሥራ ሃላፊዎችና የአካባቢው ማህበረሰብ ችግሩ የገጠማቸውን የቤተሰብ አባላት ቦታው ድረስ በመሄድ እያጽናኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

ፖሊስ በአሁኑ ወቅት የአደጋውን መንስኤ እያጣራ መሆኑን የገለጹት አዛዡ፤ ወቅቱ ደረቃማና ከፍተኛ ነፋስ የሚስተዋልበት በመሆኑ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ከመሰል አደጋዎች ራሱንና ሌሎችንም መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።