አገራዊ ምክክሩን የተሳካ በማድረግ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምእራፍ በማሸጋገር ሂደት የህዝብን አደራ በብቃት ለመወጣት ተዘጋጅተናል

82

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 14/2014(ኢዜአ) አገራዊ ምክክሩን የተሳካ በማድረግ በገለልተኝነትና በታማኝነት በማገልገል ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምእራፍ በማሸጋገር ሂደት የህዝብን አደራ በብቃት ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ የአገራዊ ምክክሩ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ተናገሩ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የሚመሩ 11 ኮሚሽነሮችን ሹመት ማፅደቁ ይታወቃል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተሿሚዎች በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮችን በምክክር መፍታት እንዲቻል የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በኮሚሽነርነት ለመምራት በህዝብ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

አገራዊ ምክክሩን የተሳካ በማድረግ በገለልተኝነትና በታማኝነት በማገልገል ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምእራፍ በማሸጋገር ሂደት ከህዝብ የተጣለባቸውን ከባድ አደራ በብቃት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ኮሚሽነሮቹ አረጋግጠዋል።

በኮሚሽኑ በአባልነት የተሾሙት አምባሳደር መሃመድ ዲሪር፤ የተሰጣቸው ሃላፊነት ከባድና ውስብስብ እንዲሁም ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ የህዝብ አደራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሂደቱ ውጤት ለማምጣት የህዝብን የልብ ትርታ በአግባቡ ማጤን ይገባል ያሉት አምባሳደሩ የሚነሱ እሳቤዎችንና ምክሮችን በመቀበል ለውጤታማነት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በአንዳንድ ጉዳዮች ልዩነቶች ቢንጸባረቁም አንድ የሚያደርጉ በርካታ መገለጫዎች እንዳሉ አንስተዋል።

በመሆኑም ከልዩነት ይልቅ ኢትዮጵያዊያንን አንድ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች በመኖራቸው ለምክክር፣ ውይይትና መግባባት ሊዘጋጁ ይገባል ብለዋል።

የኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ ሒሩት ገብረስላሴ፤ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ወቅት የሁሉንም ተሳትፎና አገልግሎት የምትሻበት መሆኑን ይናገራሉ።

በህዝብ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በትክክል ለመወጣት የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ በምክክር ሂደቱ አጀንዳዎችን ለይቶ በመቅረጽ ለውይይት በማቅረብና ሁሉም እንዲሳተፍባቸው ለማስቻል እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ አጠቃላይ ህዝቡ ኮሚሽኑን እንዲተባበር ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየትና አቋም በመያዝ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው አገረ መንግሥት ለመገንባት እንዲያግዝ በሚል የተቋቋመ መሆኑ ይታወቃል።

የኮሚሽኑ የስራ ዘመን 3 አመት ሲሆን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የኮሚሽኑን የስራ ዘመን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚራዘም ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም