በአግሮ-ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የባለሙያዎችን የስራ ክህሎት የሚያሻሽል ስልጠና ተጀመረ

111

የካቲት 14/2014/ኢዜአ/ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከዓለም የሰራተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር በአግሮ-ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የባለሙያዎችን የስራ ክህሎት ማሻሻል የሚያስችል ስልጠና መስጠት ተጀመረ።

የስልጠናው ተሳታፊዎች ከአማራና ሲዳማ ክልሎች ከፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች፣ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች፣ ከአሰሪና ሰራተኛ ድርጅቶች የተውጣጡ መሆናቸው ታውቋል።

አሰልጣኞቹ በአግሮ-ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ላይ ያገኙትን ክህሎት በቀጣይ ለሌሎች እንዲያጋሩ የሚደረግ መሆኑም ተገልጿል።

May be an image of 8 people, people standing and indoor

በስራና ክህሎት ሚኒስቴር የአዳዲስ ስራ ዕድሎችና ፕሮጀክቶች ዳይሬክተር አለምጸሓይ ደርሶልኝ፤ የሰራተኞችን የስራ ክህሎት ለማሳደግ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ሲባል በአግሮ-ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ላይ ለሚሰሩ ሰራተኞች የክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ ለማስቻል ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ለ30 አሰልጣኞች ስልጠና በመሰጠት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የስልጠናው ዋነኛ ዓላማም በግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያን ምርታማነት ለማሳደግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አግሮ-ፕሮሰሲንግ የሚፈልገውን አምራች ሃይል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሯ ይህም በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል።

በቀጣይ አራት ዓመታት ከ400 በላይ ለሚሆኑ አሰልጣኞች በተግባቦት፣ በቡድን ስራ፣ በስራ ባህል፣ በተነሳሽነትና ሌሎችም የክህሎት ስልጠናዎች ይሰጣሉ ነው ያሉት።

በዓለም የሰራተኞች ድርጅት (ILO) የፕሮ-አግሮ ኢትዮጵያ ቴክኒካል አማካሪ ሩቺካ ባሄል፤ በስራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

May be an image of 1 person and standing

በተለይ በአግሮ-ፕሮሰሲንግ ላይ የሰራተኞችን ክህሎት ለማሳደግና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት እንዲሁም በስራና ሰራተኛ መካከል ያለውን የክህሎት ክፍተት ለመሙላት ስልጠናው አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የዳበረ የስራ ስነ-ምግባር እንዲኖር ለማስቻል እንዲሁም የስራ ላይ ደህንነትን ለማስጠበቅ ስልጠናው አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል ያነጋገርናቸው ሰልጣኞች በዘርፉ የተሻለ ክህሎት ለመፍጠር ስልጠናው ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም