የግድቡ የኤሌክትሪክ ብርሃን የኢትዮጵያን ብልፅግና እና ታላቅ መሆን አይቀሬነት ማረጋገጫ ነው

80

ድሬዳዋ የካቲት 13/2014 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የኢትዮጵያን ብልፅግና እና ታላቅ መሆን አይቀሬነት ማረጋገጫ አንዱ ምዕራፍ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ።

ግድቡ ኤሌክትሪክ ማመንጨት መጀመሩ የድሬዳዋንም ሆነ የሀገራችንን ምጣኔ ሃብት ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር የተያዘው ሀገራዊ ውጥን ዕውን እንዲሆን መሰረት ይሆናል ብለዋል።
ከንቲባ ከድር ጁሃር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የመጀመሪያው የኤሌክትሪክ ርችት ከጉባ አድማስ ስር በመላው የኢትዮጵያ ሰማያት ላይ መረጨቱ ሁሉንም ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሚያስደስት ክስተት ነው።

ግድቡ  የኤሌክትሪክ  ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሁለንተናዊ  የለውጥ ጓዳና የተደላደለና የተፋጠነ ያደርገዋል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት ያጋጠሙን ሰውሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮችን ለመሻገር በአንድነት እየሰራን ነው ያሉት ከንቲባው፥ የግድቡ ኃይል ማመንጨት የህብረት ስራችን ይበልጥ እንዲፋፋም አጋዥ ጉልበት እንደሆነም ተናግረዋል።

እንዲሁም የተጀመረውን  የብልፅግና  እና የከፍታ  ጉዞ ዳር  ለማድረስ  ከመቼውም  ጊዜ በላይ በአንድነት በፅናት ለመጓዝ የሚያስችል እንደሆነም አስረድተዋል።

የሀገራችን የምጣኔ ሃብት  ሽግግር  እውን ከሚሆንባቸው  ግንባር ቀደም  ከተሞች ዋናዋ  ለሆነችው ድሬዳዋ የግድቡ ኤሌክትሪክ  ሀይል ማመንጨት ልዩ ትርጉም እንደሚኖረውም አስረድተዋል ።

እንደ ከንቲባ ከድር ገለፃ አሁንም ግድቡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ የሚፈለገውን የተሟላ ውጤት ለማግኘት የድሬዳዋ አስተዳደርና በየደረጃው የሚገኘው ህዝብ የሚያደርጉትን ድጋፍ ያጠናክራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም