ግድቡ የኢትዮጵያውያንና የመላ አፍሪካውያንን አልሞ የማድረግ ብቃት በታላቅ ከፍታ ያስቀመጠ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው

58

የካቲት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያንና የመላ አፍሪካውያንን አልሞ የማድረግ ብቃት በታላቅ ከፍታ ያስቀመጠ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትርና የግድቡ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አብርሃም በላይ አስታወቁ።

ዶክተር አብርሃም የግድቡ የኃይል ማመንጨት ማብሰሪያ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ይህ ትውልድ ለበጎና አገርን ለመገንባት ለሚጠቅም ተግባር ከጊዜና ታሪክ ጋር ግብግብ ሳይገጥም ይልቁንም ከጊዜ ጋር ታርቆ የእናቶቻችንና የአባቶቻችን ልጆች መሆኑን አሳይቷል ብለዋል።

ግድቡ ከጥንስሱ አሁን እስከደረሰበት ደረጃ ድረስ በርካቶች ዋጋ መክፈላቸውን አንስተው በአመራር ትውልዶች ቅብብል እየተገባደደ ይገኛል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የአገር ውስጥ የሙያ አቅምን ለማጎልበትና በራስ አቅም ለመገንባት ያስቻለ ወሳኝ ፕሮጀክት ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ውስብስብ የሲቪልና የኤሌክትሪክ ምህንድስና ስራዎች የተከናወኑበት መሆኑን አመልክተው ለዛሬው የመጀመሪያ ሃይል ማመንጫ ምዕራፍ ላይ ለመድረስ አስችሏል ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፖለቲካ መጠቀሚያነት ወጥቶ ወደ ሃይልና ህዝብ መጠቀሚያነት እንዲወርድ ያደረገ አመራር መፈጠሩን አውስተው ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታትቶች ከዚህ ቀድም የታዩ የአፈጻጸምና የአመራር ችግሮች የታረሙበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በእነዚህ ጊዜያት የተወሰዱ እርምጃዎች በየትኛውም ደረጃ ለሚያጋጥሙ የፕሮጀክት ችግሮች መፍትሄ አመላከካች እንደሆነም ተናግረዋል።ፕሮጀክቱ በአካካቢ ጥበቃና በቱሪዝም ልማት ጠንካራ የኢኮኖሚ ስበት ማዕከል ለመገንባት እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ትኩረት ሰጥቶ የሚያየው ፕቶጀክት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው የገለጹትዶክተር አብርሃም፤ በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ላይ በልዩ ልዩ ስራ የተሳተፉትን ባለሙያዎች አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም