ኢትዮጵያ ከፈጣሪ የተሰጣት ልዩ ጸጋ ውሃ ነው፤ ውሃዋንም ለታዳሽ ኃይል ማመንጫነት አውላዋለች

73

የካቲት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ኢትዮጵያ ከፈጣሪ የተሰጣት ልዩ ጸጋ ውሃ ነው፤ ውሃዋንም ለታዳሽ ኃይል ማመንጫነት አውላዋለች" ሲሉ የሳሊኒ ኩባንያ መስራች፣ ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ ፔድሮ ሳሊኒ ተናገሩ፡፡

የኩባንያው መስራች፣ ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ ይህን ያሉት የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጨት ማብሰሪያ መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

የግድቡን የኃይል ማመንጨት መጀመር ከኢትዮጵያዊያን ጋር እኩል የምናከብረው የደስታ ቀን ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከፈጣሪ የተሰጣት ልዩ ጸጋ ውሃ ነው፤ የተሰጣትን ጸጋ ለታዳሽ ኃይል ማምንጫ መዋል መቻሏን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሳይታለች ነው ያሉት፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጀመረው "ዘላቂ የልማት ግብ" የሚለው መርሃ-ግብር እዚህ ቦታ ላይ እውን ሆኗል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ በብዙ መከራና ፈተና ተፈትኖ ያለፈ መሆኑን በመጥቀስ፤  ብዙ ጠላት ያፈራንበት ቢሆንም በኢትዮጵያውያን ፅናት የግድቡን ኃይል ማመንጨት እውን ማድረግ ችለናል ብለዋል፡፡

እኛም የኢትዮጵያ ህዝብ ከእለት ጉርሱ ቀንሶ ባደረገው የገንዘብ መዋጮ የግድቡን ግንባታ እውን ማድረግ ችለናል ነው ያሉት፡፡

በዚህም የተቀበልነውን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት ይህንን ታላቅ ስኬት ማስመዝገብ ችለናል ነው ያሉት ፔድሮ ሳሊኒ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም