በቀይ ባህርና በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል ጠንካራ የትብብር ማዕቀፍ መፍጠር ያስፈልጋል- አቶ ደመቀ መኮንን

80

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2014 (ኢዜአ) የቀይ ባህር እና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለቀጠናዊ ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ትኩረቱን በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር ላይ ባደረገው 58ኛው የሙኒክ የጸጥታ ጉባዔ ላይ እተሳተፉ ነው፡፡

በጉባዔው የቀይ ባህር እና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለቀጠናዊ ኢኮኖሚያዊ ውህደት እና ሰላማዊ ልማት የበለጠ ድጋፍና ትብብር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው በአካባቢው የሚስተዋሉ ጽንፈኞችን ለማስወገድ አለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጠንካራ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

በቀይ ባህር እና በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል የአብዛኛውን ባለድርሻ አካላት ጥቅም የሚያስተናግድ የትብብር ማዕቀፍ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በሌላ በኩል እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ2019 የተቋቋመው የቀይ ባህር ፎረም ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር ያገለለ በመሆኑ የተሳሳተ አካሄድ መሆኑንም አቶ ደመቀ በጉባዔው ገልጸዋል፡፡

በቀይ ባህር አካባቢ የሚደርሰውን ህገ ወጥ የስደተኞች፣ የመድሃኒት እና የጦር መሳሪያዎች ዝውውር ለመግታት የተጀመሩ የጋራ ጥረቶች ሊበረታቱና ሊጠናከሩ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለምታካሂደው ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ ውይይት የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ተገቢውን እውቅና እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንዳመላከተው ጉባዔው ለሦስት ቀናት የሚቀጥል ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም