ለዘላቂ ሰላምና የጋራ መግባባት አገራዊ ምክክሩ አስተዋጽኦው የጎላ ነው

60

የካቲት 12/2014/ኢዜአ/በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣትና የጋራ መግባባት ለመፍጠር አገራዊ ምክክሩ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ተገለጸ። 

የእርቅና ሰላም አማካሪ አቶ ጋረደው አሰፋ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አገራዊ መግባባት ለማኅበራዊ፣ ምጣኔ ኃብትና ፖለቲካዊ መጎልበት ያለውን ፋይዳ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ሊደረግ የታሰበው አካታች አገራዊ ምክክር በተለያዩ ወገኖች መካከል ልዩነትን በመፍታት ለአገራዊ አንድነትና ኅብረት መሰረት ይጥላል ብለዋል።

አገራዊ ምክክሩ መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ለመያዝና ለዘመናት የነበሩ የሰላምና ሌሎች ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

"ምክክሩ ለኢትዮጵያ አስፈላጊና ወሳኝ እድል ነው" የሚሉት አማካሪው ለሰላም፣ አገራዊ መግባባት ያለውንም ፋይዳ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ማኅበራዊ እሴትና እውቀት በመጠቀም በራስ አቅም ችግሮችን በንግግር መፍታት እንደምትችል ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።

ምክክሩ በሰለጠነ፣ በእውቀትና ያለማንም ጣልቃ ገብነት ኢትዮያዊ በሆነ መንገድ ሁሉም እንዲወያይበት ተደርጎ እየተቋቋመ መሆኑ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያውያን የሚፈጠረውን መድረክ ተጠቅመው በመወያየትና የጋራ አቋም በመያዝ ለአገራቸው ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና ሊዘጋጁ ይገባል ብለዋል።

አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ሥልጠና በመስጠትና በሌሎች የተግባቦት ዘዴዎች አስፈላጊነቱ ላይ ሕዝብን በማንቃት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየትና አቋም በመያዝ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው አገረ መንግሥት ለመገንባት እንዲያግዝ በሚል ተቋቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም