በደቡብ ክልል የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያረጀ ቡና ጉንደላና እድሳት ንቅናቄ ተጀመረ

ሀዋሳ፤ የካቲት 12/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በ11 ዞኖችና ስድስት ልዩ ወረዳዎች ያረጀ ቡና ጉንደላና እድሳት ንቅናቄ መጀመሩ ተገለጸ።

ክልላዊ ንቅናቄው ከተጀመረባቸው አካባቢዎች መካከል ከምባታ ጠንባሮ እና ወላይታ ዞኖች ይገኙበታል።

ንቅናቄውን በዞኖቹ ሺሺቾ፣ቃጫ ቢራና ቦሎሶ ሶሬ ወረዳዎች በመገኘት ያስጀመሩት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ናቸው።

አቶ ኡስማን በወቅቱ እንዳሉት፤ ለቡና ምርትና ምርታማነት መቀነስ ያረጀ ቡና ማሳ በስፋት መኖር ዋናው ችግር ነው።

በክልሉ በቡና ተክል ከተሸፈነው 337 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ እስከ 40 በመቶ የሚሆነው ያረጀ ቡና መሆኑን አስታውቀዋል።

የቡና ተክሎቹ ከእርጅና ባሻገር በእንክብካቤ ጉድለት የተጎዱ በመሆናቸው የሚፈለገውን ያህል ምርት ማስገኘት አልቻሉም ብለዋል።

በዚህም ምክንያት አርሶ አደሩ ቡናን በስፋት አምርቶ ለገበያ ማቅረብ ካለመቻሉም በላይ የሀገሪቱ ከዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን አመልክተዋል።

ችግሩን ለማቃለል ዓይነተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በመንግስት ታምኖበት የቡና ጉንደላ ንቅናቄው ወደ ተግባር መሸጋገሩን ገልጸዋል።

ዘንድሮ በክልሉ ቡና አምራች በሆኑ ሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የቡና ተክል በመጎንደልና ነቅሎ በመትከል የማደስ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ 90 ሚሊዮን የተሻሻሉ የቡና ችግኝ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን አቶ ኡስማን አስታውቀዋል።

የቡና ልማቱን በየደረጃው በማስፋፋትና በማጠናከር የአምራቹን፣የንግዱን ህብረተሰብና የሀገሪቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ ቢሮው ኃላፊ ገለፃ ፤እስካሁን በክልሉ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን አርሶ አደሮች የቡና ልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ሆነዋል።

የከምባታ ጠምባሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መለሰ ሀጪሶ በበኩላቸው፤ በዞኑ 74 ሺህ አርሶ አደሮች በቡና ኤክስቴንሽን እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሆኖም አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አብዛኛው የቡና ምርት በተለያየ መንገድ እየቀነሰ በመምጣቱ የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

ይህንን ችግር ለማቃለል አርሶ አደሮች ሣይንሳዊ በሆነ መንገድ በባለሙያ ታግዘው እንዲሰሩና የስፔሻሊቲ ቡና ልማትን በተመረጡ ቃጫ ቢራ፣ሀደሮ ጡንጦ፣ቀዳዳላ ጋሜላ፣ጠምባሮ እና ላምቦያና ወረዳዎች ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የቡና ልማቱን በ3 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት እያካሄዱ ቢሆንም አብኛዛው የቡና ዛፍ በማርጀቱ ምርታማነታቸው እየቀነሰ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ በከምባታ ጠምባሮ ዞን ቃጫ ቢራ ወረዳ ምስራቅ ሌሾ ቀበሌ ቡና አምራች አርሶ አደር ሃይሌ አርጊቾ ናቸው።

ምርታማነታቸውን ለማሻሻል የአረጁ ቡናዎችን በመጎንደል በአዲስ ለመተካትና አዳዲስ ቡናዎችን ለመትከል እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ፤ ከቡና ልማቱ ባገኙት ገቢ ዘመናዊ ቤት ከመገንባት ባለፈ ስምንት ልጆቻቸውን እስከ ከፍተኛ ትምህርት በማስተማር ወደ ስራ ማሰማራታቸውን አስታውቀዋል።

አሁን ላይ በዓመት 66 ኩንታል እርጥብ ቡና እና 32 ኩንታል ደረቅ ቡና ምርት እንደሚሰበስቡ ነው ያመለከቱት።

በወላይታ ዞን ቦሎሶ ሶሬ ወረዳ ወርሙማ ቀበሌ አርሶ አደር ማሴቦ ማዴቦ በበኩላቸው፤ የቡና ምርታማነታቸውን ለማሻሻል 200 እግር ቡና መጎንደላቸውንና ለቡና ጥላ የሚሆን የሙዝ ችግኝ በመትከል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተጠቅመው እየተንከባከቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከግብርና ባለሙያዎች ያገኙትን እውቀትና በልምድ የቀሰሙትን ክህሎት ለሌሎች አርሶ አደሮች በማካፈል ውጤታማ እንዲሆኑ እያገዝኳቸው ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም