የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች ማኅበራዊ ችግሮችን ለማቃለል በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል

64

የካቲት 12/2014/ኢዜአ/ የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች የተፈጠሩ ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።

በጤና ሚኒስቴርና በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በሥነ-አዕምሮ ጤናና ሥነ-ልቦና ሕክምና ዙሪያ ሲሰጥ የነበረው የአሰልጣኞች ሥልጠና ተጠናቋል።

ከአራት ክልሎች የተውጣጡ በሥነ-አዕምሮ ጤናና ሥነ-ልቦና ዙሪያ የሚሰሩ 254 ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ሥልጠና በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ሲሰጥ ቆይቷል።

ሠልጣኞቹ ከአማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችና ከፌደራል የመጡ ናቸው ተብሏል።

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የሥነ-ልቦና ግንባታ ሥራ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።  

ሠልጣኞች ወደ ማኅበረሰቡ በሚመለሱበት ወቅት በሥነ-ልቦና ግንባታ ላይ በቅንጅት በመሥራት ማኅበራዊ ችግሮችን ሊያቀሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው በጦርነቱ የተፈጠረው ቀውስ ሰፊ ምላሽ የሚሻ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህንን ችግር ለመፍታትም ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸው በቀጣይም ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት ሰፋፊ ሥራዎች እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።

በጦርነቱ ሳቢያ የሥነ-ልቦና ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች በየአካባቢው ተንቀሳቃሽ የሕክምና ቡድን በማቋቋም የሥነ-ልቦናና የአዕምሮ ሕክምና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ከ42 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት መስጠት መቻሉንም አመላክተዋል።

ሰልጣኞች ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱም በዋናነት ባለሙያዎችን ማሰልጠንና የአካባቢያቸውን ማኅበረሰብ የመደገፍ ሥራ በትኩረት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።   

የሥልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው የተሰጠው ሥልጠና ወቅታዊና ችግር ፈቺ መሆኑን አንስተዋል።

ወደ ማኅበረሰቡ በሚመለሱበት ወቅትም በተለያየ ምክንያት የሥነ-ልቦና ችግር የገጠማቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች ወደ ነበሩበት ለመመለስ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም