አገራዊ ምክክሩን የተሳካና ውጤታማ ለማድረግ መገናኛ ብዙኃን ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው

245

የካቲት 12/2014/ኢዜአ/  አገራዊ ምክክሩን የተሳካና ውጤታማ ለማድረግ መገናኛ ብዙኃን ትልቅ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ምሁራን ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ አካታችና ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚል በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁሟል።

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የመገናኛ ብዙሃን ሚና ምን ሊሆን ይገባል በሚል ኢዜአ ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህራን ጋር 

ቆይታ አድርጓል።

በዩንቨርሲቲው የጋዜጠኝነት እና ኮሚኒኬሽን መምህሩ ዶክተር ሙላቱ አለማየሁ፤ አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን መረጃዎችን በወቅቱ ተደራሽ ከማድረግ አንፃር መገናኛ ብዙኃን በርካታ ስራዎች ይጠብቃቸዋል ይላሉ።

የምክክር ኮሚሽኑ በየደረጃው የሚያከናውናቸውን ተግባራት ተከታትሎ ለሕዝብ በማሳወቅ ዜጎች በሚካሔደው ውይይት ላይ አመኔታ እንዲኖራቸው የማድረግ ስራ ዋነኛ ትኩረታቸው ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በአገራዊ ምክክሩ ላይ ለሚሳተፉ ሁሉም አካላት ሚዲያው ድምጻቸው በትክክል የሚሰማበት ሊሆን ይገባል ሲሉ ዶክተር ሙላቱ አብራርተዋል።

በውይይት መድረኩ የሚሳተፉ አካላትን አቋም ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ሚዲያዎች ማስተናገድ አለባቸው የሚሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን መምህር ዶክተር ሳምሶን መኮንን ናቸው።

ኮሚሽኑ በሚያዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ መገናኛ ብዙኃኑ የምክክሩን መሰረተ ሃሳብ ማስረፅ፣ የምክክሩን ሂደትና ክንውኑን በሚገባው ልክ ሽፋን መስጠት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የመንግስትም ይሁን የግል መገናኛ ብዙኃን ከማንኛውም አካል ተፅዕኖ ነጻ እና ገለልተኛ ሆነው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል ዶክተር ሙላቱ፡፡

የምክክር ኮሚሽኑ በቀጣይ ወደ ስራ ሲገባ መረጃዎችን ለህዝብ ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ የሚታዩ ጉድለቶች እንዲታረሙ ለማስቻል የዘገባቸው አካል ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።

ከሌሎች አገራት ተመሳሳይ ልምዶችን በመቀመር ጭምር ለዚህ አገራዊ አጀንዳ ስኬት ሚዲያው ሊሰራ ይገባል ብለዋል ምሁራኑ።

ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽነርነት በህዝቡ ጥቆማ በእጩነት የተለዩ የ42 ሰዎች የስም ዝርዝር ይፋ መሆኑ ይታወቃል።