አትሌት ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር የራስ አል ካማህ ግማሽ ማራቶን ውድድርን አሸነፈች

583

የካቲት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) አትሌት ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በተካሄደው የራስ አል ካማህ የግማሽ ማራቶን ውድድርን አሸነፈች።

ዛሬ ማለዳ በተካሄደው ውድድር አትሌት ግርማዊት 1 ሰዓት ከ4 ደቂቃ ከ14 ሴኮንድ ኬንያዊቷን አትሌት ሄለን ኦቢሪን አስከትላ በመግባት አሸናፊ ሆናለች።

የኢትዮ ኤሌክትሪክ ክለብ አትሌት የሆነችው ግርማዊት ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም በተካሄደው 21ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የሴቶች ውድድር ሁለተኛ መውጣቷ የሚታወስ ነው።

ኬንያዊቷ አትሌት ሄለን ኦቢሪ 1 ሰዓት ከ4 ደቂቃ ከ22 ሴኮንድ ሁለተኛ ደረጃን ስትይዝ፤ሌላኛዋ ኬንያዊ አትሌት ሼይላ ቼፕኪሩይ 1 ሰዓት ከ4 ደቂቃ ከ36 ሴኮንድ ሶስተኛ ሆና ውድድሯን ጨርሳለች።

ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት ቦሰና ሙላቴ አምስተኛ ወጥታለች።

በወንዶች ውድድር ደግሞ ዩጋንዳዊው አትሌት ጃኮብ ኪፕሊሞ 57 ደቂቃ ከ56 ሴኮንድ አሸናፊ ሲሆን፤ኬንያዊው አትሌት ሮጀርስ ክዌሞይ 58 ደቂቃ ከ30 ሴኮንድ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

ሌላኛው ኬንያዊ አትሌት ኬኔት ኪፕሮፕ ሬንጁ 58 ደቂቃ ከ35 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ሰይፉ ቱራና አምደወርቅ ዋለልኝ በቅደም ተከተል አራተኛና አምስተኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

የራስ አል ካማህ ግማሽ ማራቶን ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ ነው የተካሄደው።