የገንዘብ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ከአውሮፓ ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ ጋር ተወያዩ

174

የካቲት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት የጋራ ጉባኤ በተጓዳኝ ከአውሮፓ ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ ዶ/ር አኒታ ዌበር ጋር በብራስልስ ውይይት አድርገዋል።

በወቅቱም በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ውይይት በማካሄድ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ተነስተው ውይይት ተደርጓል።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በተለይም የመድሃኒት አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራትን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይም ውይይት ተደርጓል።

መንግስት በወሰዳቸው አዎንታዊ እርምጃዎች በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ያለውን ፍላጎት ማሳየቱን የገለፁት ሚኒስትሮቹ የህወሃት የሽብር ቡድን የሚያደረገውን ግጭት ቀስቃሽ እንቅስቃሴን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በዝምታ ከመመልከት ወጥቶ ተጠያቂ ሊያደርገው እንደሚገባም ገልጸዋል።

መንግስት የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ሌሎች አጋሮች ጋር የሚያደርገውን ቀጣይ ውይይት ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚካሄድ አስረድተዋል።

በመጨረሻም በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል ወቅታዊ የመረጃ ልውውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መግባባት ላይ መደረሱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።