በመላው ዓለም የሚኖሩ የኢትዮጵያ ሴቶች አባል የሚሆኑበት የሴቶች ጥምረት ተመሰረተ

140

የካቲት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በመላው ዓለም የሚኖሩ የኢትዮጵያ ሴቶች አባል በመሆን ልምድና እውቀታቸውን በመጋራት ተጠቃሚ የሚሆኑበት የሴቶች ጥምረት ተመሰረተ።

ጥምረቱን በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዳያስፖራ ሴቶች የተመሰረተ ሲሆን እስካሁን በ11 ሀገራት 87 ኢትዮጵያዊያን ሴቶች አባል ሆነዋል ፤ 392 የሚደርሱ ደግሞ የአባልነት ፎርም በመሙላት በሒደት ላይ ናቸው ተብሏል።

በኢትዮጵያ እንዲሁም በየትኛውም ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውን ሴቶችን በአባልነት የሚያካትተው ጥምረቱ '' የዓለም የኢትዮጵያውያን ሴቶች ጥምረት '' የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

በኖርዌ የጥምረቱ መስራችና ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ኢትዮጵያ አለማየሁ፤ ለኢዜአ እንደገለጹት ጥምረቱ የተለያየ አቅም ያላቸውን ሴቶች በማሰባሰብ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ አቅማቸውን አውጥተው ጠንካራ ስራ ለመስራት የሚያስችላቸውን እድልን የሚያመቻች ነው።

በትምህርት፣ በኢኮኖሚና በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ልምድና አቅም በተደራጀ መልኩ ጥቅም ላይ በማዋል ሴቶች እውቀታቸውንና የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ የሚያግዝ መሆኑንም አስረድተዋል።

የዓለም የኢትዮጵያውያን ሴቶች ጥምረት ከባንኮችና ከሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት የሚሰራ ሲሆን በኢትዮጵያና በተለያዩ የአረብ አገራት የሚኖሩ ሴቶች ያላቸውን ችሎታ፣ እውቀትና ጉልበት ተጠቅመው የተሻለ ህይወት እንዲመሩ የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።

ጥምረቱ በአሁኑ ወቀት ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ የተለያዩ ቢሮዎች ጋር በትብብር እየሰራ ስለመሆኑም ወይዘሮ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።በጥምረቱ ወላጅ አልባ ሕፃናትን የማሳደግና በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች የመደገፍ ስራ መጀመሩንም ጠቅሰዋል።

በስዊዲን የጥምረቱ መስራች ወይዘሮ ሳምራዊት ልሳኑ፤ በመላው አለም በተለያዩ መስኮች ላይ የተሰማሩ ሴቶች በጋራ በማሰባሰብ እንዲደጋገፉ ማድረግ ተገቢና ጠቃሚነቱም የላቀ ነው ብለዋል።

ጥምረቱ ሴቶች በተበታተነ መልኩ የተሰማሩባቸውን መስኮች ወደ አንድ ላይ በማምጣት የተደራጀ አካሔድ እንዲከተሉና እንዲደጋገፉ የሚያደርግ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተለይም የተለያዩ ችግሮች ያሉባቸውና ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች ድጋፍ የሚያገኙበትና የሁሉም ትብብር በአንድ ማእከል የሚከናወንበት መሆኑን አመልክተዋል።

የዓለም የኢትዮጵያውያን ሴቶች ጥምረት በኢትዮጵያ ፈቃድ አግኝቶ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ በመሆኑ ዓላማውን በመደገፍ ሴቶች ተመዝግበው አባል እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም