በሲዳማ ክልል 2ኛ ዙር የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው

202

ሀዋሳ፣ የካቲት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል ሁለተኛ ዙር የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት እየተሰጠ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይነህ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ክትባቱ በክልሉ ለሚቀጥሉት ሰባት ተከታታይ ቀናት በጤና ተቋማትና በትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ ይሰጣል።

ከጤና ተቋማት ርቀው ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ በተቋቋሙ ጊያዜያዊ የክትባት መስጫ ማዕከላት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ለአንድ ሳምንት ያህል በዘመቻ በሚሰጠው ሁለተኛ ዙር የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት  ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይከተባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ክትባቱን በመውሰድ የኮቪድ-19 ተጋላጭነቱን በመቀነስ ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ ሃላፊነቱን እንዲወጣ በምገለጽ ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ በተሰጠው የመጀመሪያው ዙር ክትባት 780 ሺህ  ያህል ሰዎች መከተባቸውን ከጤና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።