የኢትዮጵያ የቋንቋ ልማት ፖሊሲ ዕውቅና የተሰጣቸው ቋንቋዎች የፌዴራል የስራ ቋንቋ ሆነው እንዲያገለግሉ ዝግጅት እየተደረገ ነው

225

አዳማ፣ የካቲት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የቋንቋ ልማት ፖሊሲ እውቅና የሰጣቸው ቋንቋዎች የፌዴራል የስራ ቋንቋ ሆነው እንዲያገለግሉ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከአማርኛ በተጨማሪ የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ በኢትዮጵያ የቋንቋ ልማት ፖሊሲ የተቀመጡትን ቋንቋዎች ወደ ስራ ለማስገባት በተዘጋጁ ሰነዶች ላይ በባለድርሻ አካላት ዛሬ በአዳማ ተመክሮበታል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በፖሊሲው እውቅና ያገኙ ቋንቋዎችን ወደ ስራ ለማስገባት የትርጉምና አስተርጓሚነትን ጨምሮ ሌሎች ደንቦችን ለማዘጋጀት የተለያዩ ጥናቶች ተካሂደዋል።

ቋንቋዎቹን ወደ ስራ ለማስገባትና ሀገራዊ የስራ ቋንቋ ለማድረግ ብዙ ሂደት ስለሚያስፈልግ ቅድመ ዝግጅቶቹን ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የሚኒስቴሩ የባህልና ቋንቋ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ በበኩላቸው፤ የቋንቋ ልማት ፖሊሲውን ስራ ላይ ለማዋል የተዘጋጁ ደንቦችና በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች ግኝት ውጤቶችን በግብዓት አዳብረን ተግባራዊ ለማድረግ ውይይቱ አስፈልጓል ብለዋል።

በተለይም ከአማርኛ በተጨማሪ የፌዴራል ቋንቋ እንዲሆኑ በኢትዮጵያ የቋንቋ ልማት ፖሊሲ የተቀመጡትን አራቱን ቋንቋዎች  ወደ ስራ ለማስገባት እየሰራን ነው ያሉት ወይዘሮ ወርቅነሽ፤ በዚህም ኦሮሚኛ፣ ሱማሊኛና አፋርኛ  ቋንቋዎች ፖሊሲውን የመተርጎም ስራዎች መጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።

የትግርኛ ቋንቋ የፖሊሲ ትርጉም እንዳልተጠናቀቀ ገልጸው፤ ትርጉማቸው የተጠናቀቁት ወደ ክልል ተልከው በየደረጃው ያለው ህብረተሰብ እንዲወያይበትና በትክክል እንዲገነዘበው እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ተጨማሪ ቋንቋዎቹን ወደ ስራ ለማስገባት የተለያዩ ጥናቶች መካሄዳቸውን ያመለከቱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ለዚህም ውጤታማነት ደንብ በማዘጋጀት ለሚኒስቴሮች ምክር ቤት ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ነን ብለዋል።

በሚኒስቴሩ የቋንቋ ትርጉምና ስነ ቃል ዳይሬክተር ዶክተር አውላቸው ሹምነጋ፤ ሀገራዊ የቋንቋ ፖሊሲውን ተፈፃሚ ለማድረግ የፖሊሲውን ዝርዝር ይዘት ባለድርሻ አካላት በትክክል መገንዘብ ስላለባቸው እየተመከረባቸው ነው ብለዋል።

ይህም በተለይም ከቋንቋ መጠቀም መብት፣ ከስራ ቋንቋና ትምህርት፣ ከሀገር በቀል እውቀቶችና እሴቶችን ከመጠበቅ፣ የፅሑፍ ሃብቶችን ለማከማቸትና ጠብቆ ከማቆየት አንፃር በፖሊሲው የተቀመጡ  ይዘቶችን ተግባራዊ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼