ባንኩ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን እያገዘ ነው

55

ደሴ ኢዜአ የካቲት 10/2014...የኦሮሚያ ባንክ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ አሻራውን እያኖረ መሆኑን አስታወቀ።

የኦሮሚያ ባንክ  በሦስተኛው ዙር ይመንዝሩ፤ ይቀበሉ፤ ይሸለሙ መርሃ ግብሩ ለባለድለኞች በደሴ ከተማ የተለያዩ ሽልማቶችን አበርክቷል።

የባንኩ ምክትል ችፍ ፓርትነርሽፕ አቶ በላይ በይሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ባንኩ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ የራሱን አሻራ ለማስቀመጥ እየሰራ ነው።

ለገበታ ሀገር፣ ገበታ ለሸገርና ለሌሎችም ትላልቅ ፕሮጀክቶች በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ድጋፍ ማድረጉንም ጠቁመዋል።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የ20 ሚሊዮን ብር ቦንድ በመግዛትና  1ሚሊዮን ብር በስጦታ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆን ባንኩ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል  ብለዋል።

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ለመቋቋምም እየተደረገ ላለው ጥረት ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ባንኩ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመከላከል የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት የይመንዝሩ፤ ይቀበሉና ይሸለሙ መርሃ ግብር እያካሄደ መሆኑንም አስረድተዋል።

በዚህም የሶስተኛ ዙር ባለእድለኞችን ሸልሟል ያሉት አቶ በላይ በሽልማቱ ከተካተቱት ውስጥ ሞተር ሳይክል፣ ጀኔሬተርና የተለያዩ የእጅ ስልኮች እንደሚገኙባቸው አመልክተዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ሰለሞን ደባልቄ በበኩላቸው ባንኩ ቅርንጫፉን በማስፋፋት በከተማው የሚካሄደውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በህውሓት የሽብር ቡድን የተቀዛቀዘው የንግድ እንቅስቃሴ እንዲሻሻል እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ባንኩ ደንበኞችን ተደራሽ ለማድረግ እያከናወነ ያለውን እንቅስቃሴ ከተማ አስተዳደሩ ይደግፋል ብለዋል።

ከተሸላሚ ደንበኞች መካከል ሞተር ሳይክል የተሸለመው ወጣት አደም መሐመድ እንዳለው ከውጭ የተላከለትን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ በባንኩ በመመንዘሩ ተሸልሟል።

ሌሎችም በጥቁር ገበያ እየመነዘሩ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከሚያዛቡ በህጋዊ መንገድ ከባንኮች ሊመነዝሩ እንደሚገባ መክሯል።

ሌላዋ ተሸላሚ ወጣት ልዕልና ሰለሞን በበኩሏ እህቷ የላከችላትን ገንዘብ በኦሮሚያ ባንክ በመመንዘሯ ዘመናዊ የእጅ ስልክ ተሸላሚ በመሆኗ መደሰቷን ገልጻለች፡፡

ኦሮሚያ ባንክ በሀገሪቱ በከፈታቸው ከ340 በላይ ቅርንጫፎች ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ማፍራት እንደቻለም ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም