የአፍሪካ አገራት መንግስታት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሚያደርጉትን ጥረት የአውሮፓ ህብረት ሊደግፈው ይገባል

63

የካቲት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአፍሪካ አገራት መንግስታት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሚያደርጉትን ጥረት የአውሮፓ ህብረት ሊደግፈው እንደሚገባ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ተናገሩ።

በአፍሪካ ህብረት እና በአውሮፓ ህብረት  አገራት መካከል ያለው ትብብር የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ይህን ያሉት በ6ኛው የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት የጋራ ጉባኤ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነው።

አፍሪካ በፈጣን ለውጥ ላይ ትገኛለች ያሉት ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል፤ ለውጡን ለጋራ ተጠቃሚነት ማዋል ደግሞ ከአፍሪካ ህብረት እና አውሮፓ ህብረት አባል አገራት የሚጠበቅ ነው ብለዋል።

በአፍሪካ እየታየ ያለው ለውጥ በሰላምና ደህንነት መደፍረስ እየተፈተነ እንደሚገኝም ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የአፍሪካ አገራት መንግስታት ሽብርተኝነትን በመዋጋት ሰላምን ለማስፈን እያደረጉት ያለውን ጥረት የአውሮፓ ህብረት ሊደግፍ ይገባል ብለዋል።

በአፍሪካ በርካታ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች እንዳሉ አስረድተው በተለይ በዲጂታል ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶችን ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ የፋይናንስ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት።

በመሆኑም  የአፍሪካን ልማት መደገፍ የቀጣዩን ትውልድ እጣ ፈንታ መገንባት መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም ነው ያስረዱት።

600 ሚሊዮን የሚጠጉ አፍሪካዊያን የኤሌክትሪክ ሃይል እንደማያገኙ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ አውሮፓና አፍሪካ በመሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ በጋራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

በሰላምና ደህንነት፣ በስደተኞች፣ በአየር ጠባይ ለውጥ እና በሌሎች ጉዳዮች በጋራ እንዲሰሩም ባቀረቡት የትብብር ምክረ ሃሳብ ጠይቀዋል።

አፍሪካ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት እንድታመርትና በጤናው ዘርፍ የተሟላ ተግባር ለማከናወን የምታደርገውን ጥረት የአውሮፓ አገራት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።

በአፍሪካ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የትራንስፖርት መሰረተ ልማት መስፋፋት አይነተኛ ሚና እንዳለው አስረድተው፤ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት በአፍሪካ የመሰረተ ልማት ለማስፋፋት የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ ጠይቀዋል።

የአውሮፓ ህብረት የወቅቱ ፕሬዚዳንትና የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ አፍሪካና አውሮፓ በጋራ የተሳሰረ እጣ ፈንታ አላቸው፤ በአፍሪካ ሰላምና ልማት መስፈን ለአውሮፓ አገራት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በአፍሪካ እና አውሮፓ አገራት መካከል ያለው ትብብር በጋራ ተጠቃሚነት ብሎም የሁለቱን አህጉራት የወደፊት እጣ ፈንታ በሚገነባ መልኩ መከናወን እንዳለበት ተናግረዋል

በአፍሪካ ያለውን ሰፊ አምራች ኃይል አህጉሪቱን በሚለውጡ የልማት ስራዎች ማሰማራት ደግሞ ለአፍሪካና አውሮፓ የጋራ ተጠቃሚነት ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርለስ ሚሼል፤ የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሄ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት የአውሮፓ ህብረት ይደግፈዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም