በነዳጅ ቦቴ ሲጓጓዝ የነበረ የኮንትሮባንድ ዕቃ በቁጥጥር ስር ዋለ

124

ሀዋሳ፤ የካቲት 10/2014 (ኢዜአ)፡ በነዳጅ ቦቴ ሲጓጓዝ የነበረ ግምቱ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሆነ የኮንትሮባንድ ዕቃ በቁጥጥር ስር ማዋሉን በጉምሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

 ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ በሕግ የተከለከለ ልባሽ ጨርቅ በቁጥጥር ስር የዋለው   የሰሌዳ ቍጥሩ ኮድ (3) 63528 ኢት  እና የተሳቢው ቁጥር ኮድ (3) 17794 ኢት በሆነ የነዳጅ ማመላለሻ ቦቴ መኪና ውስጥ ተጭኖ ሲንቀሳቀስ በአዳባ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ነው።

በጽህፈት ቤቱ የሕግ ተገዢነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዴሳ ለማ እንደገለጹት፤ ዕቃው የተገኘበት ቦቴ  ተሽከርካሪው መነሻውን ባሌ ዞን ሮቤ ከተማ አድርጎ  ወደ መሀል ሀገር እየተጓዘ ነበር።

ከህብረተሰቡ በተገኘ ጥቆማ በቁጥጥር ሥር ሊውል መቻሉን ተናግረዋል።፡

ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የተገመተው የኮንትሮባንድ እቃ በቁጥጥር ስር የዋለው ዛሬ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ተኩል አካባቢ  እንደሆነ አሰታውቀዋል።

አሽከርካሪውም በቁጥጥር ስር ውሎ በፖሊስ ምርመራ እየተካሄደበት እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በአዳባ ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ኮንትሮባንድ እቃን በነዳጅ ማመላለሻ ቦቴ ደብቆ ለማሳለፍ ሲሞከር ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ መሰል ህገ ወጥ ድርጊቶችን ሲመለከት በንቃት በመከታተልና ለሚመለከተው አካል በመጠቆም የዜግነት ግዴታውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም