ሳማሪታንስ ፐርስ ለኢትዮጵያ የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ

211

አዲስ አበባ የካቲት 11/2014(ኢዜአ) ሳማሪታንስ ፐርስ የተባለ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ለኢትዮጵያ የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ድርጅቱ የላከውን ድጋፍ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ተረክበዋል።

ሚኒስትሯ እንዳሉት 12 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የህክምና መሳሪያዎችን ያካተተው ድጋፍ በተለይም በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት ማቋቋሚያ ይውላል ብለዋል።  

ድርጅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮና ወረርሽኝን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

“የህክምና ቁሳቁሱ በዋናነት በአማራ ክልል ለሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና አንድ ሆስፒታልን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት የሚውል ነው ” ብለዋል።   

ድርጅቱ የህክምና ቁሳቁሱን ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር መሳሪያዎችን ሥራ ለማስጀመር ቴክኒሻኖችን በመላኩ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ስም አመስግነዋል።    

የሳማሪታንስ ፐርስ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሪያን ሌን፤ “በዚህ ወቅት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን በመቆማችን ኩራት ይሰማናል” ብለዋል።

ወደ ኢትዮጵያ ይዘን የመጣነው ድጋፍ 13 ቶን የሚሆን የኤክስሬይና አልትራሳውንድ ህክምና መሳሪያዎችን ጨምሮ ሌሎች ቁሳቁሶችን ያካተተ ነው ሲሉም ገልጸዋል።   

በቀጣይም የወደሙና የተዘረፉ ጤና ተቋማትን ወደ ሥራ ለመመለስ የሚደረገውን ድጋፍ ማገዛችንን እንቀጥላለን ሲሉም አብራርተዋል።    

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ተወካይ ጌትነት ስንታየሁ፤ በጦርነቱ ምክንያት በክልሉ 40 ሆስፒታሎች፣ 453 ጤና ጣቢያዎች፣ 1 ሺህ 850 ጤና ኬላዎች፣ አንድ ኦክስጂን ማምረቻና አንድ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ወድመው እንደነበር አስታውሰዋል።       

አሁን ላይ ከሞላ ጎደል ሁሉም ጤና ተቋማት ወደ ሥራ ቢመለሱም ሙሉ አገልግሎት እየሰጡ ነው ማለት እንደማይቻል አስረድተዋል።     

የጤና ተቋማቱ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ርብርብ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።  

ከዚህ አኳያ ሳማሪታንስ ፐርስ ያደረገው ድጋፍ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ሲሉም አክለዋል።  

ድጋፉ በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ የጤና ተቋማትን ወደ ስራ ለማስገባት የሚውል መሆኑ ተገልጿል።