መዲናዋን የሚመጥን የተግባቦት ስርአት ለመገንባት እየተሰራ ነው

63

የካቲት 10/2014/ኢዜአ/ አዲስ አበባን የሚመጥን የተግባቦት ስርአት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ባለፉት ስድስት ወራት ባከናወናቸው ተግባራት እና በቀጣይ ስድስት ወራት እቅድ ላይ ከተለያዩ ተቋማትና እና ከክፍለ ከተሞች የኮሙኒኬሽን ተጠሪዎች ጋር ተወያይቷል።

በዚህም ቢሮው በአገሪቱ በተጀመረው ለውጥና በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት በተፈጠሩ እድሎች ዙሪያ ህብረተሰቡን ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ዮናስ ዘውዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ባለፉት ስድስት ወራት ቢሮውን እንደ አዲስ የማደራጀት እና የማቋቋም ስራ ሲከናወን ቆይቷል።

አዲስ አበባ የበርካታ አለም አቀፍ ተቋማትና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ መቀመጫ እንደመሆኗ ከተማዋን የሚመጥን ተገቢ እና ትክክለኛ የኮሙኒኬሽን መዋቅር በመገንባት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

በዚህም ቢሮው ባለፉት ስድስት ወራት በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ ረገድ ስኬታማ ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል።

በተለይም በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የማህበራዊ ትስስር ገጾቹን ጨምሮ የተለያዩ የመገናኛ አውታሮችን በመጠቀም መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የሚያስፈጽማቸውን ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞችና እቅዶች እንዲሁም አፈጻጸማቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ ወቅታዊ መረጃዎችን እንዲያገኝ ማድረግ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በታቀደው ልክ ያልተከናወኑ ጉዳዮችን በመለየትም በቀጣይ ስድስት ወራት ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም