የፌዴራል ፖሊስን ዘመናዊና ክህሎት የተላበሰ የማድረግ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

57

የካቲት 10/2014 /ኢዜአ/ የፌዴራል ፖሊስን ዘመናዊ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘና ክህሎትን የተላበሰ ለማድረግ የሚሰጡ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ባለፉት ስድስት ወራት የስራ አፈፃፀሙ ላይ ተወያይቷል።

ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በስራ አፈጻጸም ግምገማ ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

ፖሊስ ባለፉት ስድስት ወራት የሕዝቡን ሠላምና ደህንነት የማስጠበቅና ወንጀለኞችን ለሕግ የማቅረብ ተግባራቱን በከፍተኛ ትኩረት ሲያከናውን መቆየቱንም ኪሚሽነር ጄኔራሉ ገልፀዋል።

በቀጣዮቹ ስድስት ወራትም ይኸው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በዋናነትም በየደረጃው ለሚገኙ የፖሊስ አባላት አስፈላጊ ስልጠናዎችን የመስጠትና አባሉን ሳይንሳዊ እውቀቶችን የማላበስ ስራ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል ብለዋል።

የጠቅላይ መምሪያው ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፈንታ በበኩላቸው መምሪያው ባለፉት ስድስት ወራት ወንጀልና የወንጀል ስጋቶችን በመቀነስና በመከላከል ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በተለይም አገርን ከወራሪዎች ነፃ በማውጣት፣ ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እንቅስቃሴን በመቆጣጠር ረገድ ቀላል የማይባል አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አንስተዋል።

በአገሪቷ በተካሔደው የመንግስት ምስረታ ላይ ጠላት ደቅኖት የነበረውን ስጋት ማክሸፍን ጨምሮ ሕዝባዊና ኃይማኖታዊ በዓላት በሠላም እንዲጠናቀቁ ማድረጉንም ጠቅሰዋል።

የፍቼ ሰላሌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብርሃም ጋዲሳ ፖሊስ ለአገርና ለሕዝብ በገባው ቃል መሰረት በአካባቢው ሠላም ለማምጣት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዋናነት በዞኑ የጥፋት ኃይሎችን ሴራ በማክሸፍ ረገድ ፖሊስ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም