"ኤች አር 6600" ረቂቅ ህግ በአፍሪካ ጉዳዮች ልዑክ በኩል የተጀመረውን የሰላም ጥረት የሚያቀጭጭ ነው

77

የካቲት 10/2014/ኢዜአ/ ኢትዮጵያን በተመለከተ የወጣው "ኤች አር 6600" ረቂቅ ህግ በአፍሪካ ጉዳዮች ልዑክ በኩል የተጀመረውን የሰላም ጥረት የሚያቀጭጭ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በማስመልከት ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልክተኛ ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ እንዲሁም የአሜሪካ መንግስት ጭምር ያሉበት የሰላም እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጽኑ አቋም እንዳላት አሜሪካ እየተረዳች በመምጣቷ የሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻሻል እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ መንግስት የአስተዳደር አካል ጋር መልካም ግንኙነት ቢኖራትም በተወሰኑ የህግ አውጭው የኮንግረንሱ አባላት  ኤች.አር 6600 ረቂቅ ህግ መውጣቱን ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያም አልፎ አፍሪካንም የሚጎዳው ይህ ረቂቅ ህግ በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴንጉ ኦባሳንጆና አሜሪካም ጭምር ያለችበትን የአፍሪካ ጉዳዮች ልዑክ የጀመረውን የሰላም ጥረት የሚያቀጭጭ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያንም ይሄንን ረቂቅ ህግ ለመቃወም "በበቃ"" ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ዘመቻ አማካኝነት እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተጀመረው ብሄራዊ ምክክር ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ባሳተፈ መንገድ ወደ አንድ አይነት የጋራ ስምምነት መምጣት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ሁሉንም አካታች የሆነው ምክክር በተወሰኑ ቡድኖች መካከል የሚደረግ ድርድር አይደለም" ያሉት አምባሳደር ዲና፤ ይልቁንስ በህዝቦች መካከል የነበረውን ልዩነት በሰለጠነ መንገድ በንግግር መፍታት የሚያስችል የሰላም መንገድ ነው ብለዋል፡፡

ከዚሁ ባሻገር ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ከድንበር ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለውን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

የመተማ ገላባት መንገድ እንደቀደመው ሁሉ ለዜጎች እንቅስቃሴ ክፍት እንዲሆን ከሱዳን መንግስት ጋር ንግግር መጀመሩንም ጠቁመዋል ቃል አቀባዩ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም