ተቋማቱ የፋይናንስ ደህንነትን ለማረጋገጥ በትብብር ለመስራት ተስማሙ

222

የካቲት 10/2014/ኢዜአ/ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እና የፌዴራል ዋና ኦዲተር የፋይናንስ ደህንነትን ለማረጋገጥ በትብብር ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ በቀለ እና የፌዴራል ዋና ኦዲተር ምክትል ዳይሬክተር መሰረት ዳምጤ የተቋማቱን ስምምነት ፈርመዋል።

በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረገው ስምምነት ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በአለም አቀፍ ደረጃ ሽብርተኝነት እንዲስፋፋ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፤ ድርጊቱ በጊዜ እልባት ካልተሰጠው ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ስጋት ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።

የዚህን ችግር አሳሳቢነት በመረዳት በአለም ላይ ከሚገኙ 107 አገራት ጋር ተቋሙ መረጃዎችን በመለዋወጥ ስራዎችን እየሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።

የወንጀል እንቅስቃሴውን ከተናጠል ይልቅ በጋራ መከላከል ውጤታማ የሚያደርግ በመሆኑ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር ጋር በጋራ ለመስራት ተስማምተናል ብለዋል።

ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ጋር በትልልቅ ግዥዎችና ኦዲቲንግ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ስምምነቱ ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በሁለቱ ተቋማት መካከል መረጃዎችን በመለዋወጥ በወንጀል የተጠረጠሩ አካላትን ወደ ህግ ለማቅረብ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም አመልክተዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው የኦዲት ግኝቶችን መሰረት በማድረግ አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ስምምነቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት የኦዲት ግኝቶችን ለፓርላማ ለማቅርብ የዓመቱን መጨረሻ መጠበቅ ግድ ይል እንደነበር አስታውሰዋል።

በመሆኑም የተደረሰው ስምምነት በቀጣይ  በየጊዜው የሚገኙ ግኝቶችን ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ሪፖርት በማድረግ አጥፊዎችን በወቅቱ ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም