ሶስተኛው የባህልና ቱሪዝም ክልል አቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባኤ በጂንካ ተጀመረ

87

ጂንካ፤የካቲት 10/2014(ኢዜአ) የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሶስተኛውን ክልል አቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባኤ በጂንካ ከተማ መካሄድ ጀመረ።
በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ፤ በክልሉ የሚገኙ ባህላዊ እሴቶች ከቱሪስት መስህብነታቸው ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል ።

በክልሉ የሚገኙ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ሰላም ለማስፈንና እርስ በርስ መቀራረብን ለማጠናከር  ጉልህ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

እነዚህ ዕሴቶች በቀጣይ ሊደረግ ለታሰበው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ስኬታማነት አስተዋጽኦቸው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቱባ የሆኑ ባህላዊ እሴቶችን ከመጠበቅ ባለፈ በጥናታዊ ስራዎች በማጎልበት ረገድ ምሁራን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ በክልሉ የሚገኙ ብሔረሰቦች ባህልና ታሪክ ላይ የተሰሩ ጥናቶች የሚቀርቡ ሲሆን በክልሉ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶች ለኢኮኖሚ ልማትና ለስራ ዕድል ፈጠራ ያበረከቱት አስተዋጽኦ እንደሚዳስስም ተመልክቷል።

በደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና በጂንካ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በሚካሄደው ሶስተኛው ክልል አቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባኤው በክልሉ የሚገኙ የዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች ምክትል ፕሬዚዳንቶችና ተወካዮች እንዲሁም የክልሉ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም