ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በብራስልስ ከአውሮፓ ህብረት አመራሮች ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል

66

አዲስ አበባ የካቲት 10/2014 /ኢዜአ/ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርልስ ሚሼል እና ከሕብረቱ ዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ዩታ ኧርፒላይነን ጋር በብራስልስ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በ6ኛው የአፍሪካ ኅብረትና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ ጉባኤ ለመሳተፍ ቤልጂየም ብራስልስ መግባታቸው ይታወቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርልስ ሚሼል እና ከሕብረቱ ዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ዩታ ኧርፒላይነን ጋር የኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ወዳጅነት በሚጠናከርበት ጉዳይ ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ በስፍራው ለሚገኘው የኢዜአ ሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በውይይታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ያለውን አሁናዊ ሁኔታ በተመለከተ ለህብረቱ አመራሮች ገለጻ ማድረጋቸውንም ነው ያነሱት።

በኢትዮጵያ ጉዳይ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት መሬት ላይ ያለውን እውነታ እንዲገነዘቡ ለማድረግ በመንግስት በኩል የተለየዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ማስታወሳቸውንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን መንግስት ያደረጋቸውን ጥረቶች ማብራራታቸውንም ሚኒስትር ዴታዋ ገልጸዋል፡፡

መንግስት በርከት ያሉ የሰላም ጥረቶችን ሲያደርግ ቢቆይም አሸባሪው ህወሓት ግን አሁንም በአፋር ክልል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየፈጸመ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራራታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ንጹሃን ዜጎችን ለሞት እየዳረገ፣ ብዙዎችን ደግሞ ከቤት ንብረታቸው እያፈናቀለ መሆኑን ጭምር እንደገለጹላቸውም ተናግረዋል፡፡  

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአሸባሪውን ቡድን ጥፋት ተገንዝቦ ሊያወግዘው እንደሚገባ መግለጻቸውንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በኢትዮጵያ የተከሰተው የድርቅ አደጋ በህብረተሰቡ ላይ ትልቅ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን በውይይቱ ላይ ማንሳታቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ አፋጣኝ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች በርካታ መሆናቸውን በመግለጽ መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ ባለፈ የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቃቸውንም ነው የገለጹት፡፡

የህብረቱ አመራሮችም የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የጀመረውን ጥረት አድንቀው፤ ጥረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

መንግስት በአገሪቱ ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳቱንም የህብረቱ አመራሮች ስለማድነቃቸው ሚኒስትር ድኤታዋ አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም