ፈጣንና ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት ለህዝቡ ለማዳረስ የተቀናጀና የተናበበ አሰራር ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል

75

አዳማ ፤ የካቲት 09/2014 (ኢዜአ) ፈጣንና ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት ለህዝቡ ተደራሽ ለማድረግ የተቀናጀና የተናበበ የጋራ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞትዮስ ገለጹ።
የፌዴራልና የክልሎች  የፍትህ ሴክተር የጋራ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ በሴክተሩ የሚታየውን የአገልግሎት አሰጣጥ ማነቆዎችን ማስወገድ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።

"ፈጣንና ቀልጣፋ የፍትህ ስርዓት ተደራሽነት ህዝቡ ከእኛ የሚጠብቅ ቀዳሚ አጀንዳ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህን እውን ለማድረግም  በመካከላችን የተቀናጀና የተናበበ የጋራ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ያስፈልገናል ነው ያሉት።

የፌዴራል ስርዓቱ መሰረታዊ መርሆዎችን በጠበቀ  መልኩ ወጥነት ያለው በህግ ዓይን ተገማች የሆነና ተቀራራቢ የፍትህ ውሳኔዎች በቅልጥፍና ሊተላለፉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የፍትህ ስርዓቱ ዜጎች የሚጎዱበት ሳይሆን እንባቸው የሚታበስበት፤ ጉልበት ያለውም ሆነ  ሀብታሙ፣ ባለስልጣኑና ደሃውን ዜጋ በእኩል ማገልገል የሚችል ብሎም ለዜጎች ዋስትና የሚሰጥ የፍትህ ስርዓትና የዘርፉን አገልግሎት ማረጋገጥ ይገባናል ብለዋል ዶክተር ጌዲዮን ።

የማህበረሰብ አቀፍ ፍትህ አገልግሎት፣ የሽግግርና የተሃድሶ ፍትህ ላይ በየደረጃው ያለው  ሴክተሩ የተቀናጀ ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑንም አመላክተዋል።

በመድረኩ ላይ ጽሑፍ ያቀረቡት በሚኒስቴሩ የክልል ጉዳዮች ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ መኮንን መሸሻ፤  የፌዴራልና የክልሎች የፍትህ ሴክተር መስሪያ ቤቶች በወንጀል ጉዳዮችና በፍትህ አሰጣጥ ሂደት ላይ የጋራ የሆነ ስምምት መድረኩ  አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ክልሎችና የፌዴራል የፍትህ ሴክተሮች በህግና ፍትህ ጉዳዮች ተቀናጀተው በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የፍትህ ስርዓቱን ከማዘመንና አሰራሮችን ከማሻሻል አንስቶ በፌዴራል የተጀመሩ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርምን ወደ ክልሎች በማውረድ ወጥነት ያለው የተቀናጀና የተናበበ ሀገራዊ አሰራር ለመዘርጋት መድረኩ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረም ተመልክቷል።

ለአንድ ቀን በተዘጋጀት የምክክር መደረክ ላይ  የፌዴራልና የክልሎች የዘርፉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም