ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአፍሪካ እና በአውሮፓ ኅብረት የጋራ ጉባኤ ለመሳተፍ ቤልጂየም ብራስልስ ገቡ

85

የካቲት 9/2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ6ኛው የአፍሪካ ኅብረትና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ ጉባኤ ለመሳተፍ ቤልጂየም ብራስልስ ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብራስልስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የአገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ጉባኤው ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን፤ የሁለቱ ኅብረቶች አባል አገራት መሪዎች፣ የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎችና ተወካዮች እንዲሁም የሁለቱ አህጉሮች የተለያዩ እንግዶች እንደሚታደሙ ይጠበቃል።  

በአውሮፓ እና በአፍሪካ ኅብረት መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገውን ግንኙነት ለማጠናከር ጉባኤው ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።

በሁለቱ ኅብረቶች መካከል ያለውን የፖለቲካ ግንኙነት በማጠናከርና ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ረገድም ትልቅ ግምት የተሰጠው ጉባኤ መሆኑን የኢዜአ ሪፖርተር ከስፍራው ዘግቧል።  

መሪዎቹ ብልጽግናን ማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የሚወያዩ ሲሆን ጎን ለጎንም የአፍሪካ-አውሮፓ የኢንቨስትመንት ፓኬጅ ይፋ ይደረጋል ተብሏል።  

ፓኬጁ ዓለም አቀፍ ችግር የሆኑትን የአየር ንብረት ለውጥና ወቅታዊ የጤና ችግር ከግምት ባስገባ መልኩ  ወደ ሥራ እንዲገባ እንደሚደረግም ይጠበቃል።     

 የአውሮፓ ኅብረትና የአፍሪካ ኅብረት የ2030 የጋራ ራዕይ ድንጋጌም በጉባኤው እንደሚፀድቅ ይጠበቃል።

በአዲስ የሠላምና የደኅንነት ማዕቀፍ ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ የአፍሪካና የአውሮፓ አገራት መሪዎች በጉባኤው ላይ በስፋት ምክክር ያደርጋሉ።

በተጨማሪም ልማትን በፋይናንስ መደገፍ፣ የጤና ሥርዓትን ማሻሻልና ክትባት ማምረት፣ ግብርናና ዘላቂ ልማት፣ ትምህርት፣ ባህል፣ የሙያ ሥልጠና ሥርዓትን ማዘመን ላይም መሪዎቹ ይወያያሉ።

ስደትና የሰዎች ዝውውር፣ የምጣኔ ኃብት ትስስር፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የኃይል ማስተላለፍ እና የትራንስፖርት ዘርፎችም የመሪዎቹ የመወያያ አጀንዳዎች ናቸው ተብሏል።  

የአውሮፓ ኅብረትና የአፍሪካ ኅብረት ግንኙነትና የጋራ ጉባኤ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2000 የተጀመረ ሲሆን ጉባኤው በየሦስት ዓመቱ ሲካሄድ ቆይቷል።

የመጀመሪያው የኅብረቶቹ ጉባኤ በግብጽ የተካሄደ ሲሆን ፖርቹጋል፣ ሊቢያ፣ ቤልጂየምና ኮትዲቯር በተከታታይ ጉባኤው የተካሄደባቸው አገራት ናቸው።

የዘንድሮው ጉባኤ እ.አ.አ 2020 መካሄድ ሲገባው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለሁለት ዓመታት ከተራዘመ በኋላ ነገ በቤልጂየም ብራስልስ ይጀመራል።

የአውሮፓ ኅብረትና የአፍሪካ ኅብረት የጋራ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ፣ የጋራ የፓርላማና የኮሚሽን ጉባኤም በመደበኛነት በተለያዩ ጊዜያት ያካሂዳሉ።

ሁለቱ ኅብረቶች የለጋሽና የተቀባይ ግንኙነታቸው ወደ ትብብር እንዲለወጥ ለማድረግ የሚያስችል የጋራ ስትራቴጂ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2007 አውጥተው አጋርነታቸውን ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም