የሕብረቱ ጉባኤ “በአፍሪካ-አውሮፓ ኢንቨስትመንት ፓኬጅ”ና በሌሎች አለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ ይመክራል

611

የካቲት 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) 6ኛው የአፍሪካና የአውሮፓ ሕብረት ጉባኤ “በአፍሪካ-አውሮፓ ኢንቨስትመንት ፓኬጅ” እንዲሁም በአፍሪካዊና በሌሎች አለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ እንደሚመክር ተገለጸ።

6ኛውን የአፍሪካና የአውሮፓ ሕብረት ጉባኤ በተመለከተ የአውሮፓ ህብረት ባወጣው መግለጫ በጉባኤው የአውሮፓና የአፍሪካ ህብረት በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ስለሚኖራቸው የጋራ ጥቅምን ያስጠበቀ ትስስር እንዲሁም የበለጸጉ አህጉሮችን ለመገንባት ስለሚቻልበት ጉዳዮች ይመክራሉ ብሏል።

በዋናነት “በአፍሪካ-አውሮፓ ኢንቨስትመንት ፓኬጅ” እና አሳሳቢ በሆነው የአየር ጸባይ ለውጥ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ነው የተነገረው።

በተጨማሪም ስለ ግብርና ምርታማነት፣ አለም አቀፍ ቀውስ እያስከተሉ ስለሚገኙ የጤና ችግሮች ጉባኤው እንደሚመክር ተገልጿል።

ስድስተኛው የአፍሪካና አውሮፓ ህብረት ጉባኤ ነገና ከነገ በስትያ በቤልጂየም ብራሰልስ ይካሄዳል።