በኢትዮጵያ የፋይናንስና ኦዲት ሪፖርቶች ደረጃቸውን እንዲጠብቁ የቁጥጥር ሥራ ተጠናክሯል

416

አዲስ አበባ የካቲት 09/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተቋማት ፋይናንስና ኦዲት ሪፖርቶች ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ የቁጥጥር ሥራውን ማጠናከሩን የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ገለጸ።

ዓለም አቀፉን የአካውንቲንግ ቀን ለመጀመሪያ ቀን በአዲስ አበባ ተከብሯል።የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ሂክመት አብደላ እንደገለጹት ቦርዱ ለሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች ፈቃድ እየሰጠ ነው።

ከተቋማት የሚመጡ የፋይናንስና ኦዲት ሪፖርቶች ደረጃቸውን ጠብቀው መከናወናቸውን የማረጋገጥና የመቆጣጠር ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አለም አቀፉን የአካውንቲንግ ሪፖርቲንግ ማእቀፍ ፈርማ ተቀብላለች ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ ቦርዱ ይህንን ስታንዳርድ ተፈጻሚ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሒሳብ ባለሙያዎች በበኩላቸው በኢትዮጵያ የፋይናንስና ኦዲት ሪፖርቶች ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በሙያቸው የተመሰከረላቸው የሂሳብና ኦዲት ባለሙያና የሂሳብና ኦዲት ሥራዎችን የሚያከናውነው ዴሊጀንስ ኮንሰልታንሲ ባለቤት አቶ ቴዎድሮስ ጥላሁን፤ የሙያዊ ሥነ-ምግበሩን ተከትለው ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ሙያዊ ሥነ-ምግባርን ያልተከተለ አሰራር ተጠያቂነትንም እንደሚያስከትል ገልጸው ሌሎችም የሒሳብ ባለሙያዎች ሥነ-ምግባርን የተከተለ አሰራር እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በአፍሪካን ሶሳይቲ ፎር ላብራቶሪ ሜዲስን የፋይናንስ ኃላፊ ወይዘሮ ነጻነት ዋሲሁን፤ የሙያ ሥነ-ምግባር በየቀኑ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ግብዓት ናቸው ብለዋል።

እርሳቸውንም ጨምሮ ባለሙያዎች ወደ ሥራ በሚሰማሩበት ወቀት በትምህርት የቀሰሙትን ተግባር ላይ እንዲያውሉት ክትትል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ሙያ የሚመራበት የሕግ ማእቀፍ አለው ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግ ትምህርት መምህሩ አቶ ስንታየሁ ደምሴ ናቸው።

ሙያው በአለም አቀፍ ደረጃ በሚወጡ ሕጎች የሚመራ መሆኑን አንስተው የዘርፉ ባለሙያዎች ወደ ሥራ ሲገቡ በእነዚህ ተቋማት የሚወጡ የሙያ ሥነ-ምግባሮችን ተከትለው መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።