የታችኛው የኦሞ ሸለቆ መካነ ቅርስን ለመንከባከብ የሚያስችል የአስተዳደር ዕቅድ ሰነድ ተዘጋጀ

169

ጂንካ፤የካቲት 09/2014(ኢዜአ) የታችኛው የኦሞ ሸለቆ መካነ ቅርስ ለመንከባከብ የሚያስችል የአስተዳደር ረቂቅ ዕቅድ ሰነድ መዘጋጀቱን የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ ።

በቅርሱ አጠባበቅ ዙሪያ ያተኮረና ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የምክክር መድረክ  በጂንካ ከተማ ተካሂዷል።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አቡቶ አሊቶ በወቅቱ እንዳሉት፤ጥንታዊ የሰው ዘር መገኛ የሆነው የታችኛው ኦሞ ሸለቆ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ቢመዘገብም እንደ አለም ቅርስነቱ ተገቢውን ጥበቃ እየተደረገለት አይደለም።

ቅርሱን መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባ አመልክተው፤  ቅርሱን ለመጠበቅና ለመንከባከብ የሚያስችል የአስተዳደር ዕቅድ ሰነድ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በአስተዳደር ዕቅድ ረቂቅ ሰነድ ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኩሴ ጉድሼ፤ ”ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዝሃ ባህሎች መገኛ ናት” ብለዋል።

የብዝሃ ባህሎች ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በማጥናት እና በመሰነድ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስተዋወቅ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ብዝሃ ባህሎች የማጥናት፣የመሰነድ ብሎም የማስተዋወቅ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቁመው፤ በቀጣይ በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የፌዴራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የመካነ ቅርስ ልማትና አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ ፀሐይ እሸቴ በበኩላቸው፤በታችኛው ኦሞ ሸለቆ መካነ ቅርስ ላይ የሚደረጉ ተፅዕኖዎች ለመከላከል የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በቅርሱ አካባቢ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ሀገራዊ ጥቅም ያላቸው ቢሆኑም ለቅርሱም ጥንቃቄና እንክብካቤ በማድረግ  ለሀገራዊ ጥቅም የሚውሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ለዚህም ቅንጅታዊ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ እንደሆነ አመልክተዋል።

በቅርሶቹ ደህንነት ዙሪያ የምርምር ስራዎችን በማከናወን ዩኒቨርሲቲው ቅርሱን የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንደሚወጣም የገለጹት ደግሞ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤሊያስ አለሙ ናቸው።

በምክክር መድረኩ የተሳተፉ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ፣ በቅርሱ ዙሪያ የሚሰሩ የልማት ድርጅቶች እና በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት የቅርሱን ደህንነት ለማስጠበቅና ለመንከባከብ በቅንጅት ለመስራት የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል።