በአማራ ክልል 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች የእለት ደራሽ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል

157

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 09/2014(ኢዜአ)  በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሃት ወረራ እንዲሁም ከኦሮሚያ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ጨምሮ 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች የእለት ደራሽ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስታወቀ።

ለነዚህ ዜጎች የክልሉ መንግስት፣ የፌደራል መንግስት፣ ዳያስፖራው፣ የኃይማኖት ተቋማትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ያልተቋረጠ ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠይቋል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ እታገኘሁ አደመ፤ ለኢዜአ እንደተናገሩት በክልሉ በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለው ከነበሩት ወገኖች መካከል አብዛኛዎቹን ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል።

አሸባሪው ህወሃት በፈጸመው ወረራ በአማራና አፋር ክልሎች በርካታ ወገኖች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ይታወሳል ።

በዚህም በአማራ ክልል ከሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ኦሮሞ ብሄረሰብ እና ዋግ ህምራ ብሄረሰብ ዞን በአጠቃላይ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ቆይተዋል።    

በህወሃት ወረራ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ከነበሩት ዜጎች መካከል አብዛኛዎቹ ወደ መኖሪያቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል።     

ከኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ቀደም ሲል ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል የመጡ 900 ሺህ ወገኖች እስካሁን ወደ ቀደመ መኖሪያቸው አለመመለሳቸውን ጠቁመው የክልሉ መንግስትም እስካሁን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ለነዚህ ዜጎች የሚያደርገውን ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።