ግጭትን ለመከላከልና ለመቀነስ የሃይማኖት ተቋማትን ሚና በሚመለከት ምክክር እየተካሔደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ግጭትን ለመከላከልና ለመቀነስ የሃይማኖት ተቋማትን ሚና በሚመለከት ምክክር እየተካሔደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 09/2014(ኢዜአ) ግጭትን ለመከላከልና ለመቀነስ የሃይማኖት ተቋማትን ሚና በሚመለከት በአዲስ አበባ ምክክር እየተካሔደ ነው።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ''ግጭትን ለመከላከልና ለመቀነስ የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው ሚና '' በሚል ነው ምክክሩን እያካሄደ ያለው።

ምክክሩ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የጉባኤውና የክልሎች የስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።
የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ የሃይማኖት መሪዎች ግጭትን በመከላከልና በመቀነስ ያላቸው ሚና የጎላ እንደሆነ አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች የጋራ መግባባት ለመፍጠር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጠይቀዋል።
በዋናነትም ግጭቶች በሚከሰቱበት ወቅት መፍትሔን ለማምጣት ግንባር ቀደም ሚናቸውን ማጎልበት እንደሚገባቸውም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በተለይ የሐይማኖት መሪዎችና አባቶች ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ አገራዊ መግባባትን ለማምጣት እንዲሰሩ ነው ጠቅላይ ጸሃፊው የጠየቁት።
በመድረኩ "አገራዊ ምክክር ለሰላምና ለአገራዊ መግባባት" ላይ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል።
በተጨማሪም በቀጣይ ስድስት ወራት የሃይማኖት ተቋማቱ ሊያከናውኗቸው በሚገቡ ተግባራትና የጋራ ዕቅድ ላይም ምክክር ይደረጋል ተብሏል።