'ኤች አር 6600' ረቂቅ ሕግን በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተደራጀ መልኩ ሊቃወሙት ይገባል

115

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 09/2014(ኢዜአ) "ኢትዮጵያን ለመጉዳት" የተዘጋጀውን 'ኤች አር 6600' ረቂቅ ሕግ በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተደራጀ መልኩ ሊቃወሙት እንደሚገባ የ’አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ /ኤፓክ/ ገለጸ፡፡

ረቂቅ ሕጉ የአሜሪካ የኮንግረንስና ሴኔት አባላት ድጋፍ እንዳይሰጡት ለማድረግ አባላቱን ማነጋገር መጀመሩንም ገልጿል።

በአሜሪካ የኮንግረንስ አባላት ቶም ማሊኖውስኪ (ኒው ጀርሲ)፣ ያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን(ሮድ አይላንድስ)ና ብራድ ሼርማን(ካሊፎርኒያ)፣ ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) 'ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት' ወይም ኤችአር 6600 በሚል ያዘጋጁት ረቂቅ ሕግ ከሰሞኑ በኮንግረንሱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ውይይት እንደተደረገበት ይታወቃል።

ኤችአር 6600 በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት ተጠያቂ ናቸው ያላቸው ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ መጣል፣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የደህንነትና የንግድ ድጋፍ እንድታቆምና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እርዳታና ብድር እንዳታገኝ ክልከላን የያዘ ረቂቅ ሕግ ነው።

ረቂቅ ሕጉ ኢትዮጵያን በዘር ማጥፋት መክሰስ አላማም ያለው ሲሆን የቪዛና ጉዞን ጨምሮ በአጠቃላይ በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ላይ ገደብ ሊጥል እንደሚችል ያስቀምጣል።

በጉዳዩ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው የ’አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’ ሊቀመንበር አቶ መስፍን ተገኑ እና የኮሚቴው አባል የሆኑት ወይዘሮ ገነት ንጉሴ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2021 በተወሰኑ የአሜሪካ የኮንግረንስና የሴኔት አባላት ኢትዮጵያን የተመለከቱ ረቂቅ ሕጎች እንዲጸድቁ ተዘጋጅተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ በዳያስፖራዎች ጥረት ሕጎቹ እንዲቀሩ አልያም ጥርስ አልባ እንዲሆኑ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

የኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ "ከዚህ በፊት ኢትዮጵያን አስመልክቶ ተዘጋጅተው የነበሩ መጥፎ ሕጎች ስብስብ ውጤት ነው፤ አንድ መጥፎ ሕግ ሊይዝ የሚችለውን ነገር ሁሉ የያዘ ነው" ብለዋል።

አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የደህንነትና የንግድ ድጋፍ እንድታቆምና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እርዳታና ብድር እንዳታገኝ ክልከላ የሚያደርግ አካሄድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ረቂቅ ሕጉ በየትኛውም መመዘኛ ኢትዮጵያንም ሆነ አሜሪካን የማይጠቅም፣ የአሜሪካን ህዝብ ሊወክልና ሊመጥን የማይችል ድርጊት መሆኑን አስረድተዋል።

የአፓክ ኮሚቴ 'ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት' ወይም ኤችአር 6600 በመቃወም ዘመቻ መጀመሩንም የድርጅቱ አባላት ተናግረዋል።

በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ-ኢትዮጵያን በየአካቢያቸው የሚገኙ የኮንግረስና የሴኔት ተወካዮቻቸውን ማነጋገር መጀመራቸውንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን የሚጎዳና ለአንድ ወገን ያደላ በመሆኑ ለኮንግረንሱ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ እንዳይቀርብና ውሳኔ እንዳይሰጥበት በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተወካዮቻቸውን ማነጋገር አለባቸው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ህግ ሆኖ የሚጸድቀው አብላጫ ድምጽ ሲያገኝ በመሆኑ ይሄንን እንዳያገኝ በኮንግረንሱ አባላት ላይ ግፊት ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለመጉዳት የሚሰሩ የኮንግረንስ አባላትና ሴናተሮችን እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር 2022 በሚደረገው ግማሽ ዓመት ምርጫ በድምጽ በመቅጣት ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ሊያደርጓቸው  ይገባልም ብለዋል።

በመሆኑም በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ድምጻቸውን በአግባቡ በመጠቀም ግልጽ የሆነ መልዕክት ሊያስተላልፉ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የ’አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’ በተጨማሪ የበቃ ወይም ‘#NoMore’ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ፤ የኢትዮ-አሜሪካውያን የእድገት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤትና ሌሎች በአሜሪካ የሚገኙ የሲቪክ ተቋማት የ 'ኤችአር 6600' ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ዘመቻ እያካሄዱ እንደሆነ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም