ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ከ574 ሺህ ኩንታል በላይ የአኩሪ አተር ተመረተ

88

የካቲት 9 2014 (ኢዜአ)  በምዕራብ ጎንደር ዞን ለፋብሪካ ግብዓትነትና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ከ574 ሺህ ኩንታል በላይ የአኩሪ አተር ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ሞገስ ጋሹ ለኢዜአ እንደገለፁት ምርቱ የተገኘው በመኽር ወቅት በአኩሪ አተር  ከለማው 28 ሺህ 300 ሄክታር መሬት ነው።

ከለማው መሬት ውስጥ 10 ሺህ ሄክታር የሚጠጋው  በባለሃብቶች የለማ ሲሆን ቀሪው በአርሶ አደር ደረጃ የተሸፈነ መሆኑንም ገልፀዋል።

በአኩሪ አተር ልማቱ ከ11 ሺህ 400 የሚበልጡ አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ 206 የሚሆኑት ደግሞ  በግበርናው ዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም የተሰበሰበውን የአኩሪ አተር ምርት አምስት ባለሃብቶችና ሰባት ድርጅቶች ለፋብሪካ ግብዓትነትና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ግዥ እየፈፀሙ ናቸው ብለዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት በ8 ሺህ ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር ለምቶ ከ14 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱንም ባለሙያው ተናግረዋል።

ከአኩሪ አተር  የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በመጨመሩ የሚለማው መሬትና የሚሰበሰበው ምርት  እድገት እያሳየ መምጣቱን  አቶ ሞገስ  ጠቅሰዋል።

በዞኑ ለአኩሪ አተር ልማት ምቹ የሆነ ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኖሩ አርሶ አደሩንና ባለሃብቱን በስፋት በማሳተፍ ምርቱን ለማሳደግ  እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ከአኩሪ አተር መፈልፈያ ማሽን እጥረት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ማሽኑን ለማቅረብ ፍላጎት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን  አቶ ሞገስ  ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም