የተሰጠን የማዕረግ እድገት ለቀጣይ ግዳጅ አፈፃፀማችን ከፍተኛ መነሳሳት የሚፈጥር ነው

85

የካቲት 8/2014/ኢዜአ/ የተሰጠን የማዕረግ እድገት ለቀጣይ ግዳጅ አፈፃፀማችን ከፍተኛ መነሳሳት የሚፈጥር ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰራዊት አባላት ገለጹ።

በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የምድር ሃይል ጠቅላይ መምሪያ የላቀ አፈፃፀም ላሳዩ የሰራዊት አባላት እውቅና እና የማዕረግ እድገት ሰጥቷል።   

በምድር ሃይል ስር በመሆን ለህልውና ዘመቻው፣ ህግ ማስከበር ዘመቻና ለህብረ- ብሄራዊ አንድነት ዘመቻዎች ቁልፍ ሚና ለነበራቸው የሰራዊቱ አመራሮች፣ አባላትና ክፍሎች ተመስግነዋል።   

በመርሃ ግብሩ ላይ የማዕረግ እድገት፣ የምስክር ወረቀት እንዲሁም የቦንድና የሜዳሊያ ሽልማትም ተበርክቷል።   

የኢትዮጵያን ህልውና በመታደግ  ትልቅ ድርሻ የተወጡ የሰራዊት አባላትን ያሰለጠኑ ማሰልጠኛዎችም የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።    

በሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት ጀነራል ባጫ ደበሌ፤ "በኢትዮጵያ መንግስት የለም አገር ፈርሷል ብሎ ለተነሳው ለአሸባሪው ህወሃት መሸነፍ፡ በምድር ሃይል ስር ያሉ ማሰልጠኛዎች ሚና የላቀ ነበር'' ብለዋል።    

ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ ስልጠና ያገኙ የሰራዊት አባላት ቁልፍ ድርሻ እንደነበራቸው ጠቁመው ይህም የሚያኮራ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

በተለይም መደበኛ ሙያተኛ ሰራዊት የሚፈጠረው አስተሳሰቡ የሚቀረጸው በማሰልጠኛ ውስጥ ነው ያሉት ጀነራል ባጫ ለዚህ የሚጠቅሙ ደንቦችና መመሪያዎች ተግባራዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የሰራዊቱ አባላት ከምንም በላይ ለአገር አንድነት መጠበቅ ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሰሩ ማድረግ ወሳኝ መሆኑም ተናግረዋል።    

አገርና ህዝብ ጠባቂውን ሰራዊት ለመከፋፈል በተለያዩ መንገዶች ወሬዎች እየተነዙ መሆኑን ጠቅሰው ለመሰል እንቅስቃሴዎች ጆሮ ባለመስጠት የጠላት ፍላጎት እንዳይሳካ ማድረግ ይገባል ብለዋል።  

በዛሬው እለት የማዕረግ እድገት ያገኛችሁ የሰራዊት አባላት በቀጣይም የላቀ አፈፃፀም እንደሚኖራችሁ የፀና እምነት አለኝ ብለዋል።

የማዕረግ እድገት ካገኙት የሰራዊት አባላት  መካከል ሌተናል ኮሌኔል እንዳለ አቤ በብርሸለቆ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተተኪ ሰራዊት በማፍራት ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።   

"የማዕረግ እድገቱ የአገር አደራ ነው የሚሉት ሌተናል ኮሌኔል እንዳለ በቀጣይ የሚጠበቅብኝን ግዳጅ ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብለዋል።    

ከአዋሽ አርባ ውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት የመጡት ሻለቃ በሽር ኢብራሂም በበኩላቸው ማዕረጉን በማግኘቴ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል በቀጣይም የበለጠ ተነሳሽነት እንዲኖረኝ ያደርጋል ብለዋል።

ወደ ማሰልጠኛው የሚመጡ ተተኪ የሰራዊት አባላት የአገር ፍቅር ስሜትን ተላብሰው እንዲወጡ የሚጠበቅብኝን አደርጋለሁ ሲሉም ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም