በጎንደር ከተማ ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ

83

የካቲት 8 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ ባለፉት ስድስት ወራት ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የከተማ አስተዳዳሩ አስታወቀ፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አራተኛ ዙር ዘጠነኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል፡፡

የአስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በጉባኤው ላይ ባቀረቡት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንዳመለከቱት፤ የኢንቨስትመንት ፈቃዱ የተሰጠው ለ76 ባለሃብቶች ነው።

ባለሀብቶቹ በከተማው በአነስተኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በግብርና ምርቶች ማቀናበር፣ በኮንስትራክሽንና ተዛማጅ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ጥያቄ ያቀረቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ባለሀብቶቹ ወደ ግንባታ ሲገቡ ከ20 ሺህ በላይ ወገኖች ቋሚና ጊዚያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ጠቁመው፣ ለባላሀብቶቹ የኢንቨስትመንት ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

አቶ ዘውዱ እንዳሉት፤ በግማሽ የበጀት ዓመቱ ከተማ አስተዳደሩ 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸውን 28 ባለሀብቶች ለማስተናገድ አቅዶ ነበር።ዘርፉን ለማሳደግ በተደረገ ጠንካራ እንቅስቃሴ ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች ፈቃድ በመስጠት ከዕቅድ በላይ ማከናወን መቻሉን አስታውቀዋል።

የከተማው ሰላም አስተማማኝ እየሆነ መምጣቱ እንዲሁም የጥምቅት በዓል በተለየ ድምቀት መከበሩ ለከተማው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መነቃቃት አስተዋጽኦ ማድረጉንም አቶ ዘውዱ ተናግረዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ትልልቅ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ይዘው ለሚመጡ ባለሀብቶች የተለያዩ ማበረታቻዎች ማዘጋጀቱን የተናገሩት ደግሞ የአስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ግርማይ ልጃለም ናቸው።

ባለሀብቱ ብሮክራሲው ሳይረዝም የግንባታ ቦታ በፍጥነት የሚያገኝበትን የአሰራር ስርዓት ከመዘርጋት ጀምሮ መሰረተ ልማት የተሟላላቸውን የኢንቨስትመንት ቦታዎች በቅድሚያ እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከተማ አስተዳደሩ አልሚ ባለሀብቶችን ከማበረታታት ጎን ለጎን ለረጅም ዓመታት መሬት አጥረው ወደ ግንባታ ካልገቡ ባለሀብቶች 24 ሄክታር የግንባታ ቦታ በመንጠቅ በፍጥነት ለሚያለሙ ባለሀብቶች መሰጠቱንም ጠቁመዋል፡፡

የከተማው ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ፀጋው አዘዘ፤ ምክር ቤቱ በቀሪ ስድስት ወራት ለከተማው ፀጥታ መጠናከርና ለመሰረተ ልማት መስፋፋት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ የዕለቱን የመወያያ አጀንዳዎች መርምሮ ያጸደቀ ሲሆን የከተማ አስተዳደሩን የኦዲት ግኝት ሪፖርት በማዳመጥ ከተወያየ በኋላ ያጸደቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም