የምክከር መድረኩ የጋራ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ወሳኝ አስተዋጽኦ ይኖረዋል

314

ድሬዳዋ ፤ የካቲት 8/2014( ኢዜአ) ሀገራዊ የምክክር መድረኩ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት ወሳኝ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገለጸ።

የድሬዳዋ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሀገራዊ ምክክር መድረኩ ላይ ያተኮረ ውይይት  ዛሬ  ከምሁራን፣ ከሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር አካሄዷል ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ብሔራዊ የምክክር መድረክ ለዘመናት ሲንከባለሉ ለነበሩ የተለያዩ አስተሳሰቦች፣ ትርክቶችና ቁርሾዎች  ሀገራዊ መፍትሄ በመስጠት  ለመሻገር እንደሚያስችል  የውይይቱ ተሣታፊዎቹ  ገልጸዋል።

ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በመገንባት  በማፅናት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ሚናው የጎላ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡

ለውይይቱ  ፅሁፍ ያቀረቡት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የፖለቲካ ተመራማሪ አቶ ሱራፌል ጌታሁን እንዳሉት፤ የሚካሄደው ሁሉን አካታች ውይይት በሀገሪቱ  የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ይረዳል፡፡

በህገ-መንግስት፣ በሰብአዊ መብት አከባበርና ማንነት ፣ በወሰን ጉዳዮች ለሚነሱ አንኳር ጥያቄዎች መፍትሄ በማፈላለግ እና የሽግግር ጊዜ ፍትህ በማስፈን  አስተዋጽኦ የጎላ  እንደሚሆንም ጠቅሰዋል፡፡

በድሬዳዋ  የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም ሰብሳቢ አቶ ዮናስ በትሩ ፤ ሀገራዊ መድረኩ ህዝብን ከህዝብ በማቃቃር ሚና በነበራቸው የተበላሹ ትርክቶች ላይ መፍትሄ ለመስጠትና ጠንካራ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዝግጅት ምዕራፍ ላይ ጠንካራ ሥራ መስራት የኮሚሽኑን  ተአማኒነት  እንደሚያጎለብተው  ነው አቶ ዮናስ  የገለጹት፡፡

“የትኛውንም አጀንዳ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ወደ ትክክለኛ መንገድ ተመልሰው በሀገር ግንባታ ላይ የድርሻቸው እንዲወጡ ብሔራዊ የምክክር መድረኩ ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል” ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር መምህራን ማህበር ሊቀመንበር አበበ  ታምራት ናቸው፡፡

የምክክር መድረኩ ሁሉን አካታችና ፍትሃዊ  በማድረግ የተሻለች ሀገር ለመገንባት ሁሉም በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

የድሬዳዋ የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ተወካይ ወይዘሮ መሪየን አባስ ፤ሊህቃን ለሀገር መሠረታዊ ችግሮች በጥናትና ምርምር የታገዙ መፍትሄዎችን  ማመላከት ላይ ያላቸውን ሚና ማሳደግ  እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

መድረኩ ሀገር ለማሻገርና ጠንካራ ሀገርን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ  የሚያግዝ መሆኑን በመገንዘብ ለውጤታማነቱ መረባረብ  እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ በበኩላቸው፤ በውይይት የሚያምን ዘመናዊና የሰለጠነ ትውልድ ለመፍጠር በኢትዮጵያ ጥላ ሥር ተሰባስቦ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ሁሉን አካታች ውይይት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በቀጣይም በሀገራዊ መድረኩ  ጠቀሜታ ላይ  በየደረጃው የሚገኘው የገጠርና የከተማ ነዋሪ ማህበረሰብ እንዲወያይበት የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል።