ሁሉም ህብረተሰብ ለሀገር ሰላምና አንድነት ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል

146

ደሴ፤ የካቲት 8/2014 (ኢዜአ) ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለሀገር ሰላምና አንድነት ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሐጅ ሙፍቲ ዑመር እድሪስ አመለከቱ፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ምክር ቤት በሀገራዊ አንድነትና ሰላም ዙሪያ ዛሬ በደሴ ከተማ የዱዓ መርሐ ግብርና የምክክር መድረክ   አካሂዷል፡፡

ሐጅ ሙፍቲ ዑመር እድሪስ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳመለከቱት፤  ሁሉም የየራሱን አመለካከትና እምነት ይዞ ለኢትዮጵያ  አንድነትና ሰላም  ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል፡፡

''ሀገርና ሰላም ከሌለ ሁሉም ነገር ይቀራል'' ያሉት ሐጅ ሙፍቲ ዑመር፤ ሁሉም እንደየ እምነቱ ተከባብሮና ተቻችሎ በመኖር የአብሮነት ባህሉንና እሴቱን ማስቀጠል እንደሚኖርበት ተናግረዋል።

''ለሀገር ሰላምና ለህዝብ አንድነት ሲባል ልዩነትን በማጥበብ አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ አተኩረን ሰላም መፍጠር ግድ ይለናል'' ብለዋል።

ለዚህም መንግስት ልዩነቶችን በውይይት እንድንፈታ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ገልጾልናል ሲሉ አስታውቀዋል።

የሃይማኖት አባቶች፣ ኡላማዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ለዘመናት የኖረውን አንድነትና አብሮነት በመስበከ ሀገር ከገጠማት ውስብስብ ችግር እንድትወጣ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

ጠቅላይ ምክር ቤቱ ለአንድነትና ሰላም አበክሮ እንደሚሰራ ሐጅ ሙፍቲ ዑመር እድሪስ አረጋግጠዋል፡፡

በጦርነቱ የተጎዱ ዜጎችን መደገፍና በዘላቂነት ማቋቋምም ከሁላችንም የሚጠበቅ ተግባር በመሆኑ የምንችለውን እናድርግ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ ሰይድ መሐመድ፤ ህዝቡ ለሰላምና አንድነት ቅድሚያ እንዲሰጥ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የወደሙ ተቋማትን መልሶ ማቋቋምና የተቸገሩትን ወገኖች  መርዳት  ከሁሉም እንደሚጠበቅ ጠቁመው፤ ''አንድነታችንን ጠብቀን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስቀጠል ይኖርብናል'' ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ ሐጅ መሐመድ ሱሩር በሰጡት አስተያየት፤  ''በመካከላችን ችግር ፈጣሪዎች ካሉ በመለየት  ለህግ ማቅረብና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን ማድረግ ያስፈልጋል'' ብለዋል።

ሀገር ከገጠማት ውስብስብ ችግር እንድትላቀቅም የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ምክር ቤቱ ከአዲስ አበባ ከተማ ሙስሊም ወጣቶች እና ''ሰውነት ይቀድማል'' ከሚባል በጎ አድራጎት ማኅበር ጋር በመተባበር በጦርነቱ ለተቸገሩ ወገኖች 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉ ተመላክቷል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም