የተፋሰስ ልማት ድርቅን በመቋቋም ምርታማነት እንዲጨምር አስችሏል

384

ሐረር ፤ የካቲት 8 /2014 (ኢዜአ) የተፋሰስ ልማት የአካባቢ መራቆትን ከመከላከል ባለፈ ድርቅን በመቋቋም የግብርና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው በምስራቅ ሐረርጌ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በዞኑ በዘንድሮው በጋ በ517 ተፋሰሶች ውስጥ እየተከናወነ የሚገኘው የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራ ከተያዘው እቅድ በላይ  መከናወኑን የዞኑ ግብርና  ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  የካቲት 7/2014ዓ.ም  በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ፤ በአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴዎች በተለያዩ አካባቢዎች የአፈር መሸርሸርን በስኬታማነት ማስቀረት ተችሏል ማለታቸው ይታወሳል።

በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የጎሮ ጉቱ ወረዳ አርሶ አደሮች በአካባቢያቸው ያካሄዱት  ልማት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት አንዱ ማሳያ ነው።

ከወረዳው አርሶ አደሮች መካከል አብዱላዚዝ ሚሊዮን እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት ባከናወኑት  የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተራቆቱ መሬቶችን  በማልማት  የንብ ማነብ፣እንስሳት ማድለብ ፣የሰብል ምርታማነትን እንዲጨምር ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል።

“ለመጪው ትውልድ አረንጓዴና የለማ  ሀገርን  ለማስረከብ  እንድንችል በተለይ በአሁኑ ወቅት የተፋሰስ ልማት ስራችንን አጠናክረን ቀጥለናል” ብለዋል።

የተፋሰስ ልማት ስራ የአካባቢመራቆትን ከመከላከል ባለፈ  ደርቀው  የነበሩ ምንጮች መልሰው መመንጨት ጀምረዋል ያሉት ደግሞ የመዲሳ ጃለላ ቀበሌ  አርሶ አደር ቀመር አብደላ ናቸው።

በለሙ ተፋሰሶች  ውስጥ  የተተከሉ እጽዋቶች በመጽደቃቸውና እርጥበታማ አየር እንዲኖር በማስቻሉ የግብርና ስራን በተሻለ መልኩ በማከናወን ድርቅን  ለመቋቋም እያስቻላቸው መሆኑን  ነው የተናገሩት።

ወጣት አቡሽ መገርሳ በበኩሉ፤ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራና በእጸዋት በተሸፈኑ ተፋሰሶች ላይ   በማህበር በመደራጀት ወደ ንብ ማነብ ስራ ለመሰማራት መዘጋጀታቸውን ገልጿል።

የተፋሰስ ልማት ከሚሰጣቸው ጠቀሜታዎች መካከል አንዱ ወጣቱ ተደረጅቶ  ከስራ አጥነት በመላቀቅ እራሱን እንዲችል ማድረግ ነው ብሏል።

የጎሮጉቱ ወረዳ ተፈጥሮ  ሃብት ጥበቃ  ባለሙያ አቶ ፈለቀ እሸቴ   እንዳሉት፤ አርሶ አደሩ ባገኘው ግንዛቤ በመታገዝ የተፋሰስ ልማት ስራን  ከዓመት ዓመት እያስፋፋ ይገኛል።

አርሶ አደሩ ከሚሰማው ይበልጥ በተግባር  የሚያየውን ነገር እንደሚቀበል ያነሱት አቶ ፈለቀ፤ በአሁኑ ወቅት ከልማቱ የተሻለ ምርት እና  ገቢም እያገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

የምሰራቅ ሐረርጌ ዞን ግብርና  ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌታሁን ንጋቱ “በዞኑ በዘንድሮ ዓመት በ517 ተፋሰሶች ላይ ከ166ሺ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ  ስራዎችን  ለማከናወን  ታቅዶ ወደተግባር ተገብቷል” ብለዋል።

በዚህም  ከ8 መቶ ሺህ በላይ አርሶ አደሮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች  እየተሳተፉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

“በምሰራቅ ሐረርጌ የተፋሰስ ልማት ስራ ካልተሰራ  ግብርናን  ምርታማ ማድረግ እንደማይቻል  አርሶ አደሩ  በመገንዘቡ በ45 ቀናት ውስጥ ከእቅዱ 112 በመቶ ማከናወን መቻሉንና  1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ዋጋ ያለው ስራ አከናውኗል” ነው ያሉት  አቶ ጌታሁን።  

የዞኑን የተፋሰስ ልማት በስፍራው የተመለከቱት የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ  ምክትል ሃላፊ አቶ ኤሊያስ ከዲር በበኩላቸው፤ አርሶ አደሩ  በመልካም ተሞክሮነት የሚጠቀስ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚያበረክተው ጠቀሜታ በተጨማሪ   ለቀጣዩ ትውልድ  የለማና አረንጓዴ  ሀገርን የማስረከብ ዓላማ ያለው በመሆኑ  ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።