በደቡብ ክልል ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች ሁለተኛ ዙር የኮሮና መከላከያ ክትባት ሊሰጥ ነው

66

ሀዋሳ፤ የካቲት 08/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች ሁለተኛ ዙር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ ክትባት በዘመቻ እንደሚሰጥ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ ፤በመጀመሪያ ዙር ዘመቻ በክልሉ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መከተባቸውን አስታውሰዋል።

ከየካቲት 10/2014 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ሁለተኛውን ዙር  ክትባት በዘመቻ  ለመስጠት  ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል ፡፡

በዚህም ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎችን  ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል።

ክትባቱ በሁሉም ዞኖችና  ልዩ ወረዳዎች በሚገኙ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎች እና ጊዜያዊ የክትባት ጣቢያዎች እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ህብረተሰቡ በተጠቀሰው ጊዜ በመገኘት  መከላከያ ክትባቱን እንዲወስድ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ህብረተሰቡ ክትባቱን በመውሰድ ቫይረሱ እያስከተለ ካለው ጉዳት እራሱን እንዲከላከል የሃይማኖት አባቶች፤ የሀገር ሽማግሌዎች እና የመገናኛ ብዙሃን ግንዛቤውን ለማሳደግ እንዲያግዙ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም