መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከዛይድ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ለመስራት ስምምነት አደረገ

250

ጎባ፣ የካቲት 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ እና በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ውስጥ የሚገኘው ዛይድ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት አደረጉ።

ዩኒቨርሲቲዎቹ ዛሬ በዌቢናር ባደረጉት ውይይት በጋራ ለመስራት የተስማሙ ሲሆን፤ የስምምነት ፊርማውን የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አህመድ ከሊልና የዛይድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ክላይቶን ማኬንዚ ፈርመዋል።

ዶክተር አህመድ እንዳሉት፤ መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና ካለው ዛይድ ዩኒቨርሲቲ ጋር ሥምምነት ማድረጉ በተፈጥሮ ሀብት፣ ቱሪዝም፣ ኢንጂነሪንግ፣ ጤናና ሌሎች ዘርፎች ላይ የሚሰራውን ስራ ለማሳደግ ያግዘዋል።

የዛይድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ክላይቶን ማኬንዚ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ በሁለቱ ተቋማት መካከል በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎቶች ላይ  በጋራ ለመስራትና ቀጣናዊ ዕድገትን ለማምጣት እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል።

ስምምነቱ ከዩኒቨርሲቲዎቹ አልፎ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወንድማማችነትና መቀራረብን ይበልጥ ለማጠናከር  እንደሚያገዝ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ልምድ በመለዋወጥ በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ለመስጠትና የምርምር ስራዎችን በስፋት ለማካሄድ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን ሽፋ ስምምነቱ ዩኒቨርሲቲው እያካሄደ የሚገኘውን የተቀናጀ ምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶችን ለማጠናከር እንደሚያግዘው ገልጸዋል፡፡

በሀገሪቷ ብዙ ጥናት ያልተካሄደባቸው እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችና ብዝሃ ህይወት እንዲሁም የቱሪዝም መስህቦች ላይ  ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ለመቅሰምና ሰፊ ምርምር ለማካሄድ ስምምነቱ ጉልህ ድርሻ እንሚኖረው ተመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼