የግል ባለኃብቶች አዳዲስ ኃሳብ አፍላቂ ወጣቶችን በስፋት ሊደግፉ ይገባል

171

አዲስ አበባ፣  የካቲት 08/2014(ኢዜአ) የግል ባለኃብቶች አዳዲስ ኃሳብ አፍላቂ ወጣቶችን በመደገፍ የሥራ ፈጠራን እንዲያበረታቱ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

ላለፉት ስድስት ወራት በኃሳብ ማበልፀጊያ ማዕከላት ሥልጠናዎችን ያገኙና ኃሳባቸውን ወደ ሥራ የቀየሩ 20 የፈጠራ ባለቤቶች ተመርቀዋል።

ተመራቂዎቹ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽንና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ዩ ኤን ዲ ፒ ጋር በመተባበር ሥራ ፈጣሪዎችን በሚደግፍባቸው መርኃ ግብሮች ተሳታፊ የነበሩ ናቸው ተብሏል።

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአዳዲስ የሥራ እድሎችና ፕሮጀክቶች ዳይሬክተር አለምፀኃይ ደርሶልኝ እንደገለጹት፤ የፈጠራ ኃሳብ ያላቸውን ወጣቶች ለማበረታታት ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየተሰራ ነው።

ወጣቶች ኃሳባቸውን ወደተግባር እንዲቀይሩ ከማስተማር ባለፈ አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር የፋይናንስ ድጋፍና የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሆነም አስረድተዋል።

የግል ባለኃብቱም የፈጠራ ባለቤቶችን በመደገፍ ለአገር በቀል ችግሮች አገራዊ መፍትሄን ለማፈላለግ የሚደረገውን አገራዊ ጥረት ሊያግዙ እንደሚገባ ነው ጥሪያቸውን ያቀረቡት።

ተመራቂዎቹ በትልቅ ባህር ውስጥ ትንሽ ጨው ጠብ ያደረጉ መሆናቸውን አንስተው አሁንም መሰል የፈጠራ ሥራዎች እንዲበራከቱ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ተመራቂ የፈጠራ ባለቤቶች በማበልፀጊያ ማዕከላት የተለያዩ ሥልጠናዎችን መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።

የክሬቲቭ ኸብ ኢትዮጵያ ማናጀር አቶ ተመስገን ፍስሃ በበኩላቸው ተመራቂዎቹ ኃሳባቸውን ወደ ተግባር መቀየር የሚያስችላቸው ሥልጠና ሲያገኙ እንደቆዩ አስረድተዋል።

ሥልጠናው ከኢንዱስትሪዎችና ከዩኒቨርሲቲዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ተመራቂ ሥራ ፈጣሪዎች በበኩላቸው ሥልጠናው ምርትና አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅና ሥራቸውን ለማስፋት የሚያግዝ እንደነበር ገልፀዋል።

የንስር አግሪ ቴክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ታደሰ አምበርብር፤ በሥልጠናው ወቅት አስፈላጊው የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ገልጸዋል።  

የፊደል የጥናት ማዕከል መሥራች ሰላማዊት አለሙ በበኩሏ በተሰማራችበት የሥራ መስክ ያለባትን ክፍተት ለመሙላትና ተፈላጊ ክህሎት እንድትጨብጥ ማስቻሉን ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም