የአገር ውስጥ ምርትን በማስፋት አገሪቱ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት እየተሰራ ነው

90

አዲስ አበባ የካቲት 08/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸውን የገቢ ምርቶች በአገር ውስጥ በመተካት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የመከላከያ ሠራዊትና ለሌሎች የፀጥታ አባላትን አልባሳትና ጫማዎች በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ለማምረት የሚያስችል የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በየዓመቱ 545 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የአልባሳት ምርቶች ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ።

በአንጻሩ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው አልባሳት 114 ሚሊዮን ዶላር እንደምታገኝና በዚህም የንግድ ሚዛን ጉድለት እንደሚታይ ገልጸዋል።

ይህን ለማስተካከል ሰፋፊ ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸው በተሰሩ ስራዎችም የተለያዩ ውጤቶች ከወዲሁ መገኘታቸውን አስረድተዋል።  

ለአብነትም ለመከላከያ ሰራዊት አባላት 1 ሚሊየን 55 ሺህ በላይ ጥንድ ጫማዎችን በሀገር ውስጥ በማምረት ለዚህ ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻሉን ጠቁመዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ718 ሺህ በላይ ጥንድ ጫማዎችን በጥራት በማምረት ለአዲስ አበባ ተማሪዎች ማቅረብ መቻሉንም ጠቁመዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም አሟጦ በመጠቀም ከውጭ የሚገባውን ምርት ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ምርት መሸፈን እንደሚቻል ገልጸዋል።

በጨርቃጨርቅ ኢንደስትሪው ያለው ሀገራዊ አቅም ከውጭ የሚገባውን የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት በአብዛኛው ሊሸፍን የሚችል መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህንንም እውን ለማድረግ መንግሥት ከዘርፉ ባለኃብቶች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም