የአፋርና የኦሮሚያ ልማት ማህበራት ለተፈናቀሉ ወገኖች 4ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረጉ

235

ሰመራ ፤ የካቲት 8/2014(ኢዜአ) የአፋርና የኦሮሚያ ልማት ማህበራት አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአፋር ክልል በፈጸመው ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች 4 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶችን ድጋፍ አደረጉ።

በድጋፍ ርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ላይ የአፋር ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶኑረዲን ሰዲቅ እንዳሉት፤  አሸባሪው ቡድን በክልሉ ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀላቸው  አርብቶ አደሮችን ህይወት ለማቆየት የዕለት  ደራሽ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።


ልማት ማህበሩ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከህብረተሰቡ ጎን የመቆም ሃላፊነቱን ለመወጣት 2 ነጥብ 5  ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ምግብና ምግብ- ነክ ያልሆኑ ቁሶች ማመቻቸቱን አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ ኢቲቻ በበኩላቸው፤ በአማራና አፋር ክልሎች የሽብር ቡድኑ ወረራ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል

በተለይም በአፋር ክልል የሽብር ቡዱኑ ጥቃት አሁንም የቀጠለ በመሆኑ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለከፋችግር እንደተጋለጡ መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

የእነዚህን ዜጎች ችግር ለማቃለል መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ ለማገዝ ልማት ማህበሩ  1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚገመቱ  የዳቦ ዱቄት፣የምግብ  ዘይት ፣ብርድ ልብስና የውሃ ማጠራቀሚያ ሮቶ  ድጋፍ ይዘው መምጣታቸውን አስታውቀዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የአፋር ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊና ከልላዊ የሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አህመድ መሀመድ፤  የአፋር ክልል ህዝብ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን ሀገሩን ከሽብር ቡድኑ ጥቃት ለመከላከል  መስዋዕትነት እየከፈለ መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪው ቡድን በክልሉ የሚፈጽመው ጥቃት ያላቆመ በመሆኑ ወገናዊ አጋርነትና ሰብአዊ ድጋፍ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የልማት ማህበራቱ ያደረጉት 4 ሚሊዮን ብር የሚገመቱት ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሶች ድጋፍ ለተጎጂ ወገኖች የእለት ችግር እንደሚያቃልል በመግለጽ በተጎጂዎቹና  በክልሉ መንግስት ስም  ምስጋና አቅርበዋል።